በምስራቃዊ ቻይና የሚኖር ባን የተባለ ወጣት ለሚያሳድጋቸው ሁለት ውሾች ባወጣላቸው "ሕገ ወጥ" ስም ምክንያት ዘብጥያ ወረደ።
በቤይጂንግ የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ባን ውሾችን እያዳቀሉ በማርባት የሚታወቅ የ30 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ሰኞ እለት ሁለት የሚያሳድጋቸው ውሾችን ፎቶ አንስቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋራ በኋላ ስማቸውን 'ቼንጉዋን' እና 'ዤግዋን' እንዳላቸው ይገልጻል።
የውሾቹ ስም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነታረኪያ ሆነ። የማንዳሪን ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሚሉት፤ የውሾቹ ስም መንግሥት እና የመንግሥት ሠራተኛ ማለት ነው።
ቼንጉዋን በከተሞች አካባቢ ተቀጥረው የሚሠሩ እና ቀላል ወንጀሎችን ለመከላከል ላይ ታች የሚሉ ሲሆኑ፤ ዤግዋን ደግሞ መደበኛ ያልሆኑ እንደ በጎ ፈቃደኛ ያሉ የማኅበረሰብ ሠራተኞች ናቸው።
ጋዜጣው እንዳተተው፤ ወጣቱ ለውሾቹ ይህንን ስም ያሸከማቸው ለቀልድ ቢሆንም የአካባቢው አስተዳደር ከዚህ ስም ውስጥ የሚፈለቀቅ ደስታ ወይም ቀልድ አልታያቸውም፤ በይበልጥ ደግሞ ቼንጉዋን ከሚለው ስም።
የዪንግዡዎ ፖሊስ "ይህ የሕግ አስከባሪ አካላትን መዝለፍ" ነው በማለት በግለሰቡ ላይ ምርመራ የጀመሩት ወዲያውኑ ነው።
አክለውም የቻይናን ሕግ አንስተው፣ አንቀፅ ጠቅሰው ዘብጢያ ያወረዱት ሲሆን፤ 10 ቀናትም እዚያው ማሳለፍ አለበት ብለዋል።
አንድ የፖሊስ ኃላፊ እንዳሉት፤ የግለሰቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ፅሁፍ "ዜጎች ላይና የከተማዋ አስተዳደር ስሜት ላይ ጉዳት የሚያደርስ" ነው።
ባንም በድርጊቱ መፀፀቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ጋዜጣው እንደዘገበው "ሕጉ መኖሩን አላውቅም ነበር፤ ሕገ ወጥ መሆኑንም አላወቅኩም" ብሏል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ነገሩ የሳቅ ጅረት ሆኖላቸው ሲሳለቁ፤ አንዳንዶቹም የትኛው ሕግ እንደሚያስቀጣቸው አልያም እንደማያስቀጣቸው ሲከራከሩ ተስተውሏል።
BBC

0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን