ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ፈተና እንደገጠመው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ በሰባት ክፍላተ ከተሞች የሚኖሩ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎችን እንደሚያገለግል የተነገረለት ፕሮጀክቱ፣ በአጠቃቀም ችግር ምክንያት እየተፈተነ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስረድቷል፡፡
ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የሞተር ዘይትና የተለያዩ ኬሚካሎችን ወደ ፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያው የሚለቁ ግለሰቦች በጣቢያው ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን፣ የባለሥልጣኑ የፍሳሽ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎችም በድብቅ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመራቸውን ወደ ማጣሪያ ጣቢያው ከሚሄዱ መስመሮች ጋር እንደሚያገናኙ አስረድተዋል፡፡ እንዲህ ባሉት ተቋማት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ዕርምጃ መውሰዱንም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከየቤቱ የሚወጡ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሾችን እየተቀበለ አጣርቶ እንዲለቅ ተደርጎ የተጋጀው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ፣ በቀን 100 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም እንዳለው ይነገራል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የቤት ውስጥ ፍሳሽ ብቻ እንዲያጣራ ወደ ተዘጋጀው ጣቢያ ጎርፍ እንደሚቀላቅሉ፣ ይህም ከአቅም በላይ በሆነ ፍሳሽ እንዲጥለቀለቅ እያደረገው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በበልግ ዝናብ ወቅት ወደ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የገባ ጎርፍ የተለያዩ ክፍሎችና በባዮሎጂካል የማጣሪያ ክፍሉ ላይ ጉዳት በማድረስ ሥራውን አስተጓጉሎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በዓለም ባንክና በመንግሥት ትብብር የተገነባው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ የከፍተኛና መለስተኛ ፍሳሽ መስመር ዝርጋታ እንደተከናወነለት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ፍሳሽን በመኪና ወይም በዘመናዊ መንገድ በፍሳሽ መስመር የማስወገድ ሥራ የሚያከናውን ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙሉ ሥርዓቱን በዘመናዊ አሠራር ለመተካት እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ አዲስ አበባን በሦስት ተፋሰሶች ከፍሎ ዘመናዊ የፍሳሽ መስመር መዘርጋት ላይ እየሠራም ይገኛል ተብሏል፡፡
በአጠቃቀም ችግር እየተፈተነ ያለው የቃሊቲ ተፋሰስ የዚሁ ክፍል የሆነው የተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ሥርዓት አካል ሲሆን፣ የምሥራቅ ተፋሰስና የአቃቂ ተፋሰስ የተባሉ ሌሎች ሁለት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አቶ ተስፋለም ገልጸዋል፡፡
ከቃሊቲ ቀጥሎ ትልቅ የሚባለው የምሥራቅ ተፋሰስ ሁለት ክፍላተ ከተሞችን እንደሚያካትት የሚናገሩት አቶ ተስፋለም፣ ባለሥልጣኑ ወደ ትግበራ ለመግባት የጥናትና ዲዛይን አማካሪ በመቅጠር ሒደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክና በመንግሥት ትብብር ተግባራዊ የሚደረገው የሁለተኛ ምዕራፍ የከተማ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሺን ፕሮግራም አካል ነው፡፡ ለዚህ ፕሮግራም የዓለም ባንክ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር የፈቀደ ሲሆን፣ የምሥራቅ ተፋሰስ የፕሮግራሙ አንዱ ንዑስ አካል ነው ተብሏል፡፡
ሌላው የተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ሥርዓት አካል አቃቂ ተፋሰስ እንደሆነ፣ በአቃቂ ተፋሰስ አንድ ክፍለ ከተማና ሌሎች አካባቢዎች የሚካተቱ እንደሚሆኑ፣ የጨፌ ንዑስ ተፋሰስና ደቡብ አቃቂ ተብሎ ለሁለት እንደሚከፈል ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡ የጨፌ ንዑስ ተፋሰስ በቀን 25 ሺሕ ሜትር ኪዩብ የማራጣት አቅም እንዳለው፣ 22 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ እንደተከናወነና ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በጀት እንደሚከናወን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የደቡብን አቃቂን ፕሮጀክት ለማስጀመር ፋይናንስ እየተፈለገ ነው ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ያልተማከሉ የፍሳሽ ማስወገጃ ጣቢያዎችንም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እያከናወነ እንደሆነ፣ ማክሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ባለሥልጣኑ በስምንት የጋራ መኖሪያ ሳይቶች 12 የማጣሪያ ጣቢያዎችን ገንብቷል፡፡ እዚያው እየተቀበሉ እዚያው የማጣራት ሥራ የሚያከናውኑት ጣቢያዎቹ በአጠቃላይ በቀን 27 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም አላቸው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጡም እንደሆነ፣ በኮዬ ፈጬም እንዲሁ በቀን 33 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ማጣራት የሚችል ጣቢያ እየተገነባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ባለሥልጣኑ ዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት የማኅበረሰቡ አጠቃቀም ከፍተኛ እንቅፋት እየሆነበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ጆንያ፣ ላስቲኮች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ አጥንት፣ ጠጠርና የተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች ወደ መስመሩ የሚለቁ ነዋሪዎች መበራከት ጉዳዩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሷልም ተብሏል፡፡
የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጓዶች ላይ የሚከደኑ የብረት ንጣፎችን ተከታትለው የሚሰርቁ መብዛታቸውም፣ ሌላው ፈተና እንደሆነ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
:-ሪፖርተር

0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን