ለመሆኑ የዘንድሮው የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ጠቅላይ ሚነስትር አብይ አህመድ ማን ናቸው

ነሐሴ 9/1967 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን በምትገኝ በሻሻ በምትባል ትንሽዬ ከተማ እንደተወለዱ ወላጅ አባታቸው አቶ አህመድ አሊ ይናገራሉ፡፡
ልጃቸው ሲወለድ አቢዮት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እንደነበርና በኋላም በማሳጠር አብይ እንዳሉት ከቢቢሲጋ በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በልጅነት ጊዜው እናትና አባቱን ሲረዳ ከሁሉም ጋር ሲወዳጅ እንዳደገም ወላጅ አባቱ አቶ አህመድ አሊ በልበ ሙሉነት መስክረውለታል፡፡
‹‹ስልጣን ላይ ስለወጣ አይደለም አሉ›› ወላጅ አባቱ ስለልጃቸው ስብእና ሲናገሩ ‹‹ስለሱ መካምነት የምነግርህ አሁን ስልጣን ላይ ስለወጣ ሳይሆን ቀድሞም መልካም ተግባር ሲከውን ስላደገ እንጂ፡፡››
አስኳላውን በሻሻ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት የጀመረው የያኔው አብዮት አህመድ ያሁኑ የኢፌድረ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ ከሌሎቹ በተለየ ነገሮችን እንደሚያስተውል፣ በዓለማዊዉም በመንፈሳዊዉም ትምህርቶች ላይ ብርቱ እንደነበርም ወንድምና አብሮ አደጎቸ መስክረዋል፡፡
ከልጆች ጋር ከመጫወት ይልቅ ከትልልቅ ሰዎች ጋር ጊዜአቸውን ሲያሳልፉት እንደነበር የመሰከሩላቸው ወንድማቸው ከአንደበታቸው የሚወጡት ቃላትም እንደ ትልልቅ ሰዎች የበሰሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
የያኔው ወጣት ያሁኑ ጎልማሳው ጠቅላይ ሚኒስትር መንበረ ስልጣናቸውን ከመያዛቸው በፊት ሸምጋይ እንደነበሩም አብሮ አደጎቻቸው ይመሰክራሉ::
ወንድማቸው እንዲህ ይላሉ ‹‹ሁለት ወንድማማቾች ቢጣሉ አስታራቂያቸው አብይ ነበር፡፡ ሰላም እንዲፈጠር ያደርግ ነበር፡፡›
ዶክተር አብይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ባልደረባቸው ልታገባ ስትል ሸምግልና እንደተላኩ መስክራለች፡፡
እዚህ ላይ ጂማ አካባቢ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ሸምግለው መፍታታቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህ ደግሞ ሃገራትን፣ አባቶችን እና ህዝቦችን ሸምግለው አስታርቀዋል፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ በሁለት ሲኖዶሶች ትመራ የነበረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሽምግልና ቆመው ወደ አንድነቷ እንድትመለስ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ህዝበ ሙስሊም መካከል ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃርም በእሳቸው ሽምግልና አማካኝነት ሊፈታ ችሏል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው መቃቃርም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካኝነት እርቀ ሰላም ወርዷል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲፈጠር እና ቀጣናው በምጣኔ ሃብታዊ ትስስር እንዲጎለብት ያደረጉት አስተዋፅኦም ፍሬአማ እየሆነ መጥቷል፡፡
በደቡብ ሱዳን መሪ እና ተፎካካሪ መካከል ተደጋጋሚ ስምምነት ተፈርሞ ፊርማው ሳይደርቅ ይፈጠር የነበረው ግጭት አሳቸው ካስማሟቸው በኋላ እርቀ ሰላም ሊወርድ ችሏል፡፡
በሱዳን መፈንቅለ መንግስትን ተከትሎ በወታደራዊ ምክርቤቱ እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የነበረው እሰጥ አገባም እልባት ያገኘው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት መሆኑን ሱዳናውያኑ በይፋ መስክረውላቸዋል፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የተፈናቃዮች ቁጥር ቢጨምርም የኋላኋላ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአከናወኗቸው በጎ ተግባራት ጎን ለጎን በተለይም በህግ ማስከበሩ ስራ ላይ ክፍተት እንደሚታይ ተችዎች ሲገልፁ ይሰማል፡፡




Post a Comment

0 Comments