የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢራቅ ውስጥ ባለው ተቃውሞ ምክንያት እየጠፋ ያለው የሰው ህይወት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፡፡



ድርጅቱ በኢራቃውያን ላይ ግድያ የፈፀሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡


ላለፉት ተከታታይ አምስት ቀናት የባግዳድ እና ሌሎች የኢራቅ ከተሞች የሃገሪቱን መንግስት በሚቃወሙ ወጣት ኢራቃውያን መሞላታቸውን ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡

የአብዛኞቹ ኢራቃውያን ወጣቶች የተቃውሞ ምክንያት ደግሞ የስራ አጥነት ችግር፣ ሙስና እና ደካማ የመሰረተ ልማት አቅርቦት መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እንደ አልጀዚራ ዘገባ በዓለም አራተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ባላት ኢራቅ በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውሃ አቅርቦት በጣም ዝቅኛ ነው፡፡

ኢ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልም ኢራቃውያኑን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ሊያጎርፋቸው እንደቻለ ሲ ቢ ሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ይህን ችግር ምክንያት በማድረግ ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ የሃገሪቱን መንግስት በመቃወም አደባባይ የወጡት ኢራቃውያኑ ተቃውሟቸውን እንዲያቋርጡ በሃገሪቱ ፖሊስ አማካኝነት በአስለቃሽ ጭስ እና በውሃ የተደገፈ ብተና እየተደረገባቸው ነው፡፡

"ከዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ተመርቀን ብንወጣም ስራ አጥተናል፣ ሙሰኛች መጠየቅ አለባቸው፣ ስለተቃወምን በመንግስት በኩል ጥቃት እየተፈፀመብን ነው::" ሲሉ ኢራቃውያኑ ተቃዋሚዎች ለዲ ደብሊው(ዶቼ ቨለ) ገልፀዋል፡፡

ማክሰኞ በጀመረው በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ አማካኝነት መቶ የሚጠጉ ኢራቃውያን በአልሞ ተኳሽ ማለትም በስናይፐር እና በተለያዩ መንገዶ ሲገደሉ 4ሺዎቹ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል አልጀዚራ አስነብቧል፡፡
ሶስት ሃገራት ማለትም ኩዌት፣ ኳታርና ባህሪየን ዘጎቻቸው ወደ ኢራቅ እንዳይጓዙ እና ኢራቅ ውስጥ ያሉትም በአፋጣኝ እንዲወጡ አዝዘዋል ሲል ሲ ቢ ሲ ኒውስ ጠቅሷል፡፡

በኢራቅ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ተልእኮ ዋና ሃላፊ የሆኑት ጀኒነ ኸኒስ ፕላስ ቻርት በአምስት ቀናት ውስጥ ግድያና ጉዳት ተከስቷል፤ ያ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትም ለህግ ሊቀርቡ እንደሚገባም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Post a Comment

0 Comments