ቱርክና ሩስያ የኩርድ ታጣቂዎችን ከሶሪያ ድንበር እንዲርቁ ለማድረግ ተስማሙ፡፡


ሃገራቱ የተስማሙት የኩርድ ታጣቂዎች አሁን ካሉበት ስፍራ 30ኪሎ ሜትር እንዲርቁና አካባቢውም በሁለቱም ሃገራት ጥምረት ለመቆጣጠር ነው፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት ነበር በሰሜን ሶሪያ የነበሩ 1ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ስፍራውን ለቀው በወጡ ማግስት ቱርክ አሸባሪ ባለችው የኩርድ ወታደር ላይ በምድር ጦር እና በአየር ሃይል ጥቃት የጀመረችው፡፡
ቱርክ ‹‹ደህንነቱ የተጠበቀ›› ስፍራ ለመፍጠር በሚል በርካታ ሶርያውያን ስደተኞች በሚገኙበት ሰሜን ሶሪያ ላይ ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ ስትጀምር የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አላ አሳድ ወታደራዊ ዘመቻውን ለመከላከል ከኩርድ ታጣቂዎች ጎን በመቆም ወታደራዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡
አሁን ደግሞ ቱርክና ሩስያ የኩርድ ታጣቂዎችን ከሶሪያ ድንበር እንዲርቁ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ሃገራቱ የተስማሙት የኩርድ ታጣቂዎች አሁን ካሉበት ስፍራ በ150 ሰዓታት ውስጥ 30ኪሎ ሜትር እንዲርቁና አካባቢውም በአንካራና በሞስኮ ጥምረት ለመቆጣጠር ነው ተብሏል፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ረሲብ ጣይብ ኤርዶሃን በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ ላይ ካደረጉት የስድስት ሰዓታት ውይይት በኋላ በቱርክ ድንበር አካባቢ የሚገኙት የኩርድ ታጣቂዎች ስፍራዉን በስድስት ቀናት ውስጥ ለማስለቀቅ መስማማታቸውን ሁለቱም መሪዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
በአንፃሩ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ኢድሊብ የሚገኘውን ጦር ሲጎበኙ ቱርክ የሶሪያን ሃብት ለመቀራመት መቋመጧን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ለወታደሮቹ ረሲብ ጣይብ ኤርዶሃን ከአይ ሲስ ጋር በመሆን የሶሪያን ፋብሪካዎች እና ነዳጅ ዘርፈዋል፤ አሁን ደግሞ መሬታችንን ሊወሩ አሰፍስፈዋል ሲሉም ገልፀውላቸዋል፡፡
የሩስያ ወታደሮች እና የሶሪያ ድንበር ጠባቂዎች በጋራ የኩርድ ታጣቂዎችን አሁን ካሉበት ቦታ 30 ኪሎ ሜትር እንዲርቁ ማድረግ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
የሩሲያ እና የቱርክ ስምምነት የአካባቢው ውጥረት ይበልጥ እንዲጨምር የሚያደርግ ነው ስትል ደግሞ አሜሪካ ስምምነቱን ተቃውማለች፡፡
ፒቢኤስ እና አልጀዚራ እንደዘገቡት

Post a Comment

0 Comments