ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል አለ ኮሚቴው


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን ሲረከቡ ለመገናኛ ብዙሃን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው የኖቤል ኮሚቴ ገልጿል።


ኮሚቴው ይህን ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣይ ሳምንት ሽልማታቸውን ለመቀበል ወደ ኦስሎ ሲያቀኑ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ እንደማያደርጉ መግለፃቸውን ተከትሎ ነው።


ዶክተር አብይ ይህን ማለታቸው ተከትሎ በኮሚቴው በኩል ትችት እንደቀረበባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።


በተለይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለሀያ አመታት የቆየውን ጥላቻ በሰላም እንዲፈታ ላደረጉት ጥረት ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው ያስታወሰው ዘገባው ለወትሮው የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ሽልማቱን ህዳር 30 ከመረከባቸው አንድ ቀን ቀደም ብለው ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የተለመደ ነው ብሏል።


አብይ አህመድ (ዶ/ር) ግን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደማይሰጡ ለኖርዌዩ ኖቤል ኬሚቴ አሳውቀዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎችን እንደማይቀበሉ እና በየዓመቱ ህፃናት በሰላም ኖቤል ማዕከል ሙዚየም ላይ የሚያቀርቡትን መርሃ ግብር ላይ እንደማይገኙም ተገልጿል።


በመሆኑም በኮሚቴው በኩል ትችት እየቀረበባቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ባያደርጉ ችግር አለው ወይ ተብለው የተጠየቁት የኮሚቴው ዋና ፀሐፊ ኦላቭ ጆልስታድ "አዎ፤ በኦስሎ በሚኖራቸው ቆይታ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ እንዲኖራቸው በእጅጉ እንሻለን።" ብለዋል።


"ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ነፃና ገለልተኛ ፕረስ የሰላም አካል ስለመሆናቸው ጠንካራ እምነት አለን።" ማለታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።



ከ10 ዓመት በፊት የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ የነበሩት የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በመርሃ ግብሩ ላይ ቢሳተፉም ጋዜጣዊ መግለጫ አለመስጠታቸውን ያስታወሰው ዘገባው
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አበይት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሳተፋሉ ተብሏል።



የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም
"የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ትኩረት በሚሹበት ወቅት የሃገር መሪ ለቀናት እንዲቆዩ ማድረግ እጅግ ፈታኝ ነው።" ሲሉም ለሮይተርስ ተናግረዋል።




Post a Comment

0 Comments