ፌደሬሽኑ የኢፌዴሪ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯን ጨምሮ አምባሳደሮች እና የኤጀንሲ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተመሰረተው።
የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሰው ኃይል ማብቃትና ለኤጀንሲዎች ፈቃድ መስጠትን ጨምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀው በአሰራር ችግሮች ምክንያት በተፈለገው መንገድ እንዳይሰራ ሆኗል ብለዋል።
በመሆኑም በጋራ በመሆን ለመፍትሔው እየሰራን ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
ፌዴሬሽኑ ለስራችን ብሩህ መንገድ የሚከፍት ነው ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ መንግስት ፌዴሬሽኑን ይደግፋል ብለዋል።
የተነጣጠሉ ሃሳቦች ወደ አንድ በማምጣት የጋራ ኃላፊነት እንዲኖር እና በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት እንደሚረዳ የፌደሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰይድ አህመድ ለዋልታ ገልፀዋል።
በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን እንዳደረጉ የገለፁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ አእምሮ መምህሩ አበባው ምናየ(ዶ/ር) ፌደሬሽኑ ሲመሰረት እንዳሉት ከኢትዮጵያ የሚሄዱ ሰሪዎች በውጭ ሃገር እንዴት መስራት እንዳለባቸው በቂ እውቀት የላቸውም ብለዋል።
የተለያዩ ሃገራት በዚሁ ስራ አማካኝነት ሙያን በመሸጥ ገቢያቸውን እያሳደጉ ነው ያሉት አበባው ምናየ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግን ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ አናሳ ነው ብለዋል።
"የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት በርካታ ቤተሰብን እየረዳ የውጭ ምንዛሪን እያስገኘ ያለ ዘርፍ ነው ያሉት ዶክተሩ የሰራተኞችን ደህንነት በማስጠበቅ የስምሪት ሂደቱን ማዘመን ያስፈልጋል" ብለዋል።
ወደ ውጭ ሃገር ሄደው የተመለሱ ባለሙያዎችንም ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። በመሆኑም በቅንጅት የሚሰራ የተደራጀ አሰራር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን