‹‹አዳም የት ነህ›› ቴዎድሮስ ካሳሁን Teddy Afro



ከሩቅ ይሰማኛል የቤተስኪያን ደወል
ነብስን የሚያማልል ልብን የሚያባብል
እንደ አዲስ የሆነ እንደ አዋጅ የሆነ
ከቀን ሁሉ ጠዋት እሁድ የገነነ
ከእለት ሁሉ ግእዝ እሁድ የገነነ
ማለዳ ሰንጥቆ የሚያስገመግም ሰመመን
መሳይ ድምፅ ከሩቅ የሚሰማ
ቀላቅሎ የያዘ የካህና ወረብ የካህናት ዜማ
ነፋስ ይሚያመጣው አልፎ አልፎ ሽው የሚል
ተነስ ቀድስ የሚል አዳም የትነህ የሚል
አፍላ ጠዋት ሆኖ ሰማይ ከመሬት ጋር ሊላቀቅ ሲደማ
ሳሮች እንዳጤዙ ምንጩ ሳይነከር
ቀኑ አዲስ እንዳለ
ከማለዳ ወፎች ድምፅ በልጦ
በነፋስ ከሚጋጩ የዛፎች ድምፅ በልጦ
ከሩሩሩቅ የሚመጣው የደወል ቤት ጩኸትየካህናት ዜማ
አየሩን ሰንጥቆ ንጋት ላይ ሲሰማ
ተንስ ሲል ገና ልቤን አሸፈተው
የቆየ ስሜቴን ማህሌት ያደረ የቄስ አፍ ሸተተው
ደሞ ምስላቸው የቄሶቹ አቋቋም አደራደራቸው
የተክለ ዝማማ ሸንበቆ ስልታቸው
ባይነ ህሊናዬ ድቅን እያለብኝ ቅዝዝ ያደርገኛል
አዳም የት ነህ ይለኛል
እንዲህ ሲነጋጋ እሁድ ሊሆን ቀኑ ሰማይ ወገግ ሲል
ከደብሩ ምሶሶዎች የውስጠኛው ክፍል
ከታቦት ማደሪያው ያጎበር ክፍልፋይ ከጣሪያው ስእልስር
ልቆ ለመሰማት በሚጥር ትናጋ የዜማ ውድድር
ባንገታቸው ዙሪያ አግድም ባሰመረው የቄሶቹ ደም ስር
የሽቅብ ተገፍቶ የሚወጣው ዜማ
ጮሆ ንሮ ንሮ ልቆ ንሮ ንሮ ድንገት ፀጥ
እያለ በሚቆየው ፋታ
የጣነ ሞገሩ ወዲህ ወዲያ እንክርት ልዩ ቅጭልጭልታ
በመሃል ብቅ ሲል የሚሰጠው ሰላም የሚፈጥረው ደስታ
በጆሮዬ ነፍሶ አሁን እስኪመስል ድንግጥ ያደርገኛል
አዳም የት ነህ ይለኛል
ወዲያው ደግሞ ድንገት እጣን በነካካ የካህናት መዳፍ
ተገልጦ ከተኛው የብራና መፅሃፍ
ከቀይ እና ጥቁር የፊደላት ቆሎ
ባይን እየዘገኑ ላንቃ ላይ ወርውሮ
ከሰማያት አንባ ከአራያም ሰፈር
ተጭኖ ደመና በዜማ መሳፈር
መሄድ መሄድ መሄድ መሄድ ያሰኘኛል
መዝለቅ ካድማሱ ስር
ከፀባኦት አንባ አረያም ቅጥር
ብቻ እንደጥንቱ ሁሉ ለመሆን ያማረኛል
ያኔ ቅስናዬ ሳይፈርስ ለብዙ ዘመናት
በድንግልናዬ እንደፅናሁ ሁሉ ሰርክ ሳደገድግ ከደብር ሳልጠፋ
ከቅዳሴ ምላሽ ከፀበል ዳር ቆሜ
ድውያን ላሰልፍ ስደክምስለፋ
ነብሴን ላለመልም ስጋዬን ሳደክም እንደኖርኩት ሁሉ
እንደያኔው ሁሉ ለመሆን ያምረኛል
ደግሞ ባፍላነቴ በልጅነት ግዜ ማለዳ ነቅቼ
በሳር ውስጥ ባለ ቀጭን መንገድ በልጅ እግሬ ሮጬ
ከደብሩ ጉብታ ከደወል ቤት ኼጄ
በላብ የጠቆረ ገመድ ስወዘውዝ
እጄ አልደርስ እያለኝ በእግር ጣቴ ቆሜ
የቤቱን ወጋግራ ጉጥ ፈልጌ ስይዝ
በልጅነት የሆንኩት አኳሗኔ ሁሉ ድቅን ይልብኛ
አዳም የት ነህ ይለኛል
ዳሩ ምን ሊፈይድ የከሰመ እጣ
ግዜ አልፎበት ጥኡምነቱን ያጣ
አውራጅ ያጣ ቋንጣ
መቼም ይህቺ ህይወት መስቀሏ ብዙ ነው
ታግላ ላትረታ ፀሯን ላታስገብረው
ካለም ጋር ግብግብ ትወዳለች
ተመንትፋ ልትሄድ ለኑሮም ሳትመች
ዛሬ እኔ ቅስናዬ ፈርሶ
ድንግልናዬ ተድሶ
ጥምጣሜን ከፈታሁ ስንት ዘመን አለኝ
እንድያው ብቻ ድንገት የጥዋቱ ደወል ማለዳ
ቀስቅሶ አዳም የት ነህ አለኝ
እናም አውቆ የተኛን ሰው አይሰማም እንዲሉ
የዛሬውን ደወል አልሰማሁም አሉ
የኔ ትዝታዎች የድሮ ቀኖቼ እንግዲህ ዝም በሉ
ልቤ እንዳደላችው ለስጋዬ አሁን አለም ቁብ እንዳላት
ልትመለስበት ለነብሴም ቀን አላት
እስኪሆንላት ይኼ እንዳይብስባት
የድሮ ቀኖቼ እየነካካችሁ አትሁኑብኝ ጠላት
ልሸፋፈን እና አውቄ ልተኛበት
የዛሬውን ደወል አልሰማሁም ልበል
የደብር እድገቴ የቄስ ሁኔታዬ ትዝታዬም ዝምበል
ግን ከሩቅ ይሰማኛል የቤተስኪያን ደወል
ነፋስ ይሚያመጣው አልፎ አልፎ ሽው የሚል
ተነስ ቀድስ የሚል
አዳም የት ነህ የሚል


 


Post a Comment

0 Comments