![]() |
የአዲስ አበባ ፖሊስ መስቀል አደባባይ
ላይ ጉልበት ሲጠቀም
|
ብዙ ጊዜ ብዙ አዝነን ልባችን ተሰብሯል!
(ፖሊስ_በራሱ_ሊመረመር_ይገባል!)
(ፖሊስ_በራሱ_ሊመረመር_ይገባል!)
ሰዎች በገዛ አገራቸው ተዋርደዋል፤ ተዘርፈዋል፤ ተደፍረዋል፤ ተገድለው በየ ጥሻው እና በየ መንገዱ ተጥለዋል፡፡
በሃገራችን በቅርቡ የመጣው የፖለቲካ ለውጥ ቀድሞ ከነበረበት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ስጋት አላቅቆ ያሻንን እንድንተነፍስ እድል እንደሰጠን አይካድም፡፡
መገናኛ ብዙሃንም የሰዎችን ብሶት ‹‹ያለ ስጋት›› ለህዝብ እና መንግስት ሲያቀርቡ ተመልክቻለሁ፡፡ ለዚህም ቀድሞ ይጠላና ይወገዝ የነበረው ብሔራዊ ጣብያችንም(ኢቲቪ ማለቴ ነው) በሚገርም ፍጥነት ተቀይሮ ከህዝብ ጎን መቆሙ አንዱ ማሳያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ (ተቋሙ የሚቀሩት በርካታ ስራዎች እንዳሉ ሳይረሳ)፡፡
ያጥፉም አያጥፉም ከሃገር ወጥተው ጠብ መንጃ ያነገቱ እና በሃሳብ ይቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ጠብ መንጃቸውን ፈትተው ወደ ሃገር ገብተው አይተን ተገርመናል ፤ በኢትዮጵዊነት ባህልም ተቀብለን አስተናግደናል፡፡
ይህን ሁሉ ባደረጉ በእነ ዶክትር አብይ እና ከእሳቸው ጎን በቆሙ ኢትዮጵውያን ተደንቀን ‹‹በርቱ›› ብለናል(ያላሉ እና ያኮረፉ እንዳሉ ሳይዘነጋ)፡፡ ቢሆንም ግን፤ ቢሆንም ግን ሁሉም ነገር ገደብ እና አደብ ያስፈልገዋል እና ሃይ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ መንግስት ሰባኪ ብቻ ሆኖ ሊያልፋቸው አይገባም!
ከምንም በላይ ደግሞ በዱላ ብቻ ሚያምነው የሃገራችን #ፖሊስ በደንብ ሊፈተሸ የግድ ይላል! በሰለጠኑ ሃገራት ላይ አንድም ሰው ያለ ምክንያት መግደል እንደነውር ይቆጠራል፡ ቸልም ሲባል ሰምቸም አላውቅም፡፡
በሃገራችን ግን በርካቶች ድንገት ሲረግፉ፣ ሲደፈሩ፣ ሲጨፈጨፉ፣ ሲረገጡ ለደህንነታቸው ዋስትና ያደረጉት #ፖሊስ መግለጫ ከመስጠት የዘለለ ነገር ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡
እስከሚገባኝ #የፖሊስ ተግባር ወንጀልን መከላከል እንጂ የተፈፀመዉን ወንጀል ቆጥሮ ማውራት አይደለም!
ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ሆይ! እነዚህ ዘግናኝ ወንጀሎች ከተረጋጉ በኋላ #ፖሊስን በደንብ መመርመር አለብህ ብየ በፅኑ አምናለሁ፡፡
ስነ ምግባርን የሚያስጠብቅ ስነምግባርን የተማረ(ያወቀ) ነው እና የተማረ #ፖሊስ ያስፈልገናል!! ይህን ሳያደርጉ ‹‹ሰላም ሰላም›› ማለት ከልፈፋ ውጭ ሰላምን አያመጣም እና ጊዜ ሳይሰጠው #ፖሊስ በራሱ ሊመረመር ይገባዋል! ካልሆነ ሰላም ወዳዶች በነውረኞች እየተረገጡ እንዲኖሩ መፍቀድ ይሆናልና መላ ይሻል፡፡
0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን