የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት የቀረበለትን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን፣ ሐሙስታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለየ ሁኔታ የጋለ ክርክር አካሂዶ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።
በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው የሕወሓት አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ መፅደቅ የለበትም በማለት ከፍተኛ ክርክርአድርገዋል። የወሰንና የማንነት ጉዳይን የሚመለከት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ በመሆኑ ተመሳሳይ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ ሊሰጥአይገባም ሲሉ ሞግተዋል።
አዋጁን በማፅደቅ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ማድረግ ሕገ መንግሥቱን በሁለት መንገድ እንደሚጣረስ አውስተው፣ አንድም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን በመንጠቅ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያልተከተለ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ መሆኑን በመጥቀስተከራክረዋል።
የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት የምክር ቤቱ አባል አቶ አጽብሃ አረጋዊ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመግለጽ ከተከራከሩ በኋላ፣‹‹በቀላሉ እንደሚፀድቅ እርግጠኛ ነኝ፣ ነገር ግን የሚያመጣውን ጣጣ ቆም ብለን ብናይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ አጽብሃ ይህንን መናገራቸው በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ላይ ቁጣን ፈጥሯል። ከእነዚህም መካከል የአዴፓ አባል የሆኑት የምክር ቤቱ አባል አቶ አጥናፍጌጡ ይገኙበታል።
አቶ አጥናፍ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ጣጣ ያመጣል፣ አደጋ አለው የሚሉ ኃይለ ቃሎችና ማስፈራሪያዎችን መናገር ለዚህ ምክር ቤት አይመጥንም፣›› ሲሉየግሳፄ ይዘት ያለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አዋጅ ለውጡ ያመጣው ዕድልና ለአገሪቱ ሕዝቦች ሰላም የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል።
ኮሚሽኑን እንዳይቋቋም የሚፈልጉ ወገኖች ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱ የማይሸፍናቸውን የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ጭምር ወደኋላ ሄዶ ያያል ከሚል ሥጋትእንደሚቃወሙት ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ ወደ ኋላ ሄዶ ሕገ መንግሥቱ የማይሸፍናቸውን ጉዳዮች ጭምር ሊመረምር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በረቂቁ ላይ ዝርዝር ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የፓርላማው የውጭ ግንኙነትና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባየኮሚሽኑ መቋቋም ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣረስ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣን እንደማይጋፋ ተናግረዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴው በኩል በረቂቅ አዋጁ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ መደረጉን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ኮሚሽኑ መረጃ የመሰብሰብ፣የመተንተንና ለሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ብቻ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነበት ምክረ ሐሳቡን ሊቀበል እንደሚችል፣ በራሱ መንገድም ተመሳሳይ ኃላፊነት ያለው ኮሚሽን ወይም ተቋምእንዳያቋቁም የሚከለክለው ነገር ባለመኖሩ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣረስ አስረድተዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ሲኮላሹ የሕገ መንግሥት ጥሰት ጥያቄ ሳይነሳ፣ ለሰላም ፋይዳያለው ኮሚሽን እንዳይቋቋም የሕገ መንግሥት መጣረስን እንደ ምክንያት ማቅረብ እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክረዋል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በቂ ክርክር እንደተደረገ ገልጸው ፓርላማው ወደ ድምፅ መስጠት የተሸጋገረ ሲሆን፣ በስብሰባው የታደሙት 33 የሕወሓት አባላትየተቃውሞ ድምፅ ሰጥተዋል።
አራት የደኢሕዴን አባላት ደግሞ የተዓቅቦ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅአዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
ምንጭ፡- ሪፖርተር

0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን