የዊኪሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከሰባት ዓመታት የጥገኝነት ጊዜ በኋላ በብሪታኒያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል



ለአሳንጅ ቅርበት አለው የተባለ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል፡፡

በወዳጅ እና ደጋፊዎቹ ስለእውነት የሚሟገት ለእውነት የቆመ ጀግና፤ በተቺዎቹ ልሳን ደግሞ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ይፋ በማድረግ የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የጣለ ዝና ፈላጊ ተደርጎ ይገለፃል፤ የ47 ዓመቱ አወስትራሊያዊ የዊኪሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ፡፡

በተለይም ለባልደረቦቹ አሳንጅ ማለት የኮምፒውተር ምስጢራዊ ኮዶችን የመስበር ከፈተኛ አቅም ያለው ብልህ ባለሙያ ነው፡፡ ይህም የበርካታ ሃገራትን ምስጢር በመበርበር ለህዝብ ይፋ በማድረግ አሳይቷል፡፡

በፈረንጆቹ 1995 በመረጃ ብርበራ ተከሶ ለእስር ተዳርጎ የነበረው እና በገንዘብ መቀጫ ከእስር የወጣው አሳንጅ እ.አ.ዘ.አ ከ2006 ጀምሮ እሱ በከፈተው ዊኪሊክስ ላይ በሚያትማቸው ምስጢራዊ ሰነዶች እና ምስሎች ዝናው እየናኘ በአንድ በኩል ድጋፍ በሌላ በኩል ደግሞ ዛቻ ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡

በተለይም እ.አ.አ በ2010 የአሜሪካ ወታደሮች 18 ኢራቃውያንን በሄሊኮፍተር ተኩሰው ሲገድሉ የሚያሳየው ምስል ይፋ ካደረገ በኋላ የአለም መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ሆኖ ከርሟል፡፡

መረጃውን ይፋ ባደረገበት ተመሳሳይ ዓመት ጁሊያን አሳንጅ ለማስተማር ወደ ስቶክሆልም በመሄድ በተማሪ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል ስትል ስዊድን በመክሰሷ ለንደን  በሚገኘው ኢኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት በመጠየቅ ሰባት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በኤምባሲው ውስጥ በጥገኝነት ኖሯል፡፡

የኋላ ኋላ አስጠጊዋ ኢኳዶር አሳንጅ አሁንም ተደጋጋሚ ጥፋት መፈፀሙን አላቆመም ስትል ጥገኝነቱን ሰርዛ ለለንደን ፖሊሶች አሳልፋ ሰጥታዋለች፡፡

ይህን ተከትሎም ኢኳዶር አለም አቀፍ ህግን ጥሳለች ሲል ዊኪሊክስ ከሷታል፡፡
እንግሊዝ በበኩሏ አሳንጂ ጀግና አይደለም ማንም ደግሞ ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡

ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ ስጋቱን የገለፀው አሳንጂ ኢኳዶር የሞት ፍርድ ለሚበይኑበት ሃገራት አሳልፋ እንደማትሰጥ ምላሽ ሰጥታዋለች፡፡

በተመሳሳይ ድርጊት የአሜሪካን መረጃዎች በመበርበር ለዓለም ይፋ ያደረገው ኤድዋርድ ስነውደንን ያስጠለለችው ሩስያ የአሳንጅ መብት እንደሚከበር ተስፋ አደርጋለሁ ብላለች፡፡

ኤድዋርድ ስነውደን በበከኩሉ የኢኳዶር መንግስት የብሪታንያ ፖሊስ እንዲይዘው ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ ክስተቱ በፕረስ ነፃነት ላይ ጨለማው ሁነት ነው ሲል በትዊተር ገፁ አስነብቧል፡፡

ለአሳንጅ ቅርበት አለው የተባለ በኢኳዶር ረጅም ዓመታት የኖረ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል፡፡

ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ለንደን ወደ ሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ በመመላለስ አሳንጅ ጋር ግንኙነት ያደርግ እንደነበር የገለፀችው ኢኳዶር ለምርመራ በቁጥጥር ስር አውየዋለሁ ብላለች፡፡

የአሳንጅ መታሰርን ተከትሎ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል ሲሉ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ስለላ ድርጅት MI5 የቀድሞ ባልደረባው አኒ ማቹን ተናግረዋል::  

አር ቲ ዘግበዋል፡፡
  

Post a Comment

0 Comments