የሱዳኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በመጪው ሳምንት ለፍርድ ይቀርባሉ



ከኦማር አልበሽር በተጨማሪም 41 የቀድሞ ባለስልጣናት ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡


በተለይም በዳርፉሩ ግጭት ምክንያት ስማቸው በመጥፎ የሚነሳው ኦማር አልበሽር ሱዳንን ለ30 ዓመት ያክል በርእሰ ብሔርነት መርተዋል፡፡

በእርሳቸው የአገዛዝ ዘመን በተለይም ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ህዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የ75 ዓመቱ አዛውንት በህዝባቸው የበረታ ተቃውሞ እና በሃገሪቱ ወታደር ድጋፍ ከስልጣን ከመነሳታቸው ከሁለት ወር በፊት እንኳን ለምን ተቃወማችሁ በሚል ምክንያት እስካሁን ከ200 በላይ ሱዳናውያን ተገድለዋል፡፡

ሙስና እና አሸባሪዎችን መደገፍ ኦማር አልበሽር የሚተቹበት ዋነኛ ወንጀሎች ናቸው፡፡
እሳቸው ከስልጣን ተነስተው እንኳን በሱዳናውያኑ ተቃዋሚዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ ሊያባራ አልቻለም፡፡

የኑሮ ውድነት ለተቃውሞ አደባባይ ያስወጣቸው ሱዳናውያኑ ህዝባዊ መንግስት ስልጣኑን እስካልተረከበ ድረስ ከአደባባይ ንቅንቅ አንልም በማለት ውሎ አዳራቸውን አደባባይ ካደረጉ አምስት ወራትን አሳልፈዋል፡፡

ስልጣኑ በፍጥነት ወደ ሲቪል ሊተላላፍ ይገባል፤ ሱዳን በወታደራዊ ኃይል መመራት የለባትም ሲሉም በሃገሪቱ የጦር ቢሮ ፊት ለፊት እና በየ አደባባዮቹ ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ምላሹ ግድያ ሆኖባቸዋል፡፡

የሃገሪቱ ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሙስና፣ አሸባሪዎችን በገንዘብ መደገፍ፣ ለድጋፍ ተብሎ የሚላክ የውጭ ምንዛሪን የግል መጠቀሚያ በማድረግ እንዲሁም ህዝባዊ ተቃውሞን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማፈን በሚሉ ወንጀሎች ተጠርጥረው በመጪው ሳምንት ፍርድቤት ይቀርባሉ ብሏል፡፡

ከቀድሞው ርእሰ ብሔር በተጨማሪም በ41 የቀድሞ ባለስልጣናት ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡


Post a Comment

0 Comments