ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት አምቦ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ
============================
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ እና የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነዋሪዎችን እያወያዩበት ባለው የአምቦ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

ከምዕራብ ሸዋና ከአካባቢው የተመረጡ ነዋሪዎች ጋር በአበበች መታፈሪያ ሆቴል ውይይት እየተካሄደ ሲሆን፤ ከሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውጪ እንዲሁም በከተማዋ ጎዳና ላይ በርካታ የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ ድምጽ እያሰሙ እንደሆነ አንድ የአምቦ ነዋሪ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ነዋሪው እንደገለፁት፤ ጠዋት ወደ ሆቴሉ ቅጥር ግቢ በመግባት በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የሞከሩ ወጣቶች በመከልከላቸው ውጥረቱ ተፈጥሯል።

በከተማዋ ዋና ጎዳና እና በሆቴሉ ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያና የኦሮሚያ ፓሊስ አባላት ያሉ ሲሆን፤ ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ሰምተናል።

በኦሮሚያ ሠሞኑን ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ በአምቦ ከተማ አንድ የ80 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትናንት ከሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችም ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

ቢቢሲ አማርኛ

Post a Comment

0 Comments