ሱዳን የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፓርቲን የሚያከስም ህግ አፀደቀች


ህጉ የኦማር አልበሽርን ፓርቲ ለመበቀል የወጣ ሳይሆን የሱዳናውያኑን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣ ነውም ተብሏል፡፡


ሱዳናውያኑ የዳቦ ዋጋ መናርንና የኑሮ ውድነትን አስታክከው የጀመሩት ህዝባዊ ተቃውሞ ጥያቄአቸው ምላሽ እያገኘ መጥቷል፡፡


ሱዳንን ለሰላሳ ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ሲመሯት የነበሩትን ኦማር አልበሽርን ከስልጣን አስነስተው ወህኒ እንዲገቡ ካደረጉ ወራት አልፈዋል፡፡

በሱዳናውያኑ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ ነበር ከተባሉት የ75 ዓመቱ አዛውንት በተጨማሪ እሳቸው የሚመሩት ናሽናል ኮንግረስ (ኤን ሲ ፒ) የተባለው ፓርቲያቸውም የሚከስምበት እጣ ፈንታ ፊቱ ላይ ተደቅኗል፡፡

ሮይተርስ ከሰዓታት በፊተ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ውሳኔው የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አደርጎ የተላለፈ እና የሽግግር መንግስቱ በአልበሽር የመሪነት ጊዜ የነበረውን እስላማዊ እንቅስቃሴን ወደ ሱዳን ተቋማት ለማስረፅ የተደረገውን አካሄድ ለማስቀረት ያለውን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡

ሮይተርስ የሱዳን መንግስት ቴሌቪዥንን ጠቅሶ አንደዘገበው ፓርቲው ከመክሰሙም በተጨማሪ ንብረቱም እንዲያዝ መወሰኑ የፍትሕ ሚኒስትሩ ነስረዲን አብደልባሪ ገልፀዋል፡፡

በሱዳን የኦማር አልበሽርን መንግስት ተቃውመው ወጡትን በማበረታታት ተቃውሞው እንዲጎለብት ሲያደርግ የቆየው የሱዳን ‹ፕሮፌሽናል አሶሲየሽን›(ኤስ ፒ ኤ) አዲሱን ህግ ተቀብሎታል፡፡
‹‹ህጉ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ህዝባዊ መንግስት እንዲኖር የሚያደርግ እርምጃ ነው፡፡›› ሲልም ድጋፉን ገልጿል፡፡

ህጉ ረጅም ከተባለው እና 14 ሰዓታትን ከፈጀ የሱዳን ሉዓላዊ ምክርቤት እና ካቢኔ ጉባኤ በኋላ የጸደቀ ነው፡፡

የሃገሪቱ የመረጃ ሚኒሰትር ፈይሰል ሞሐመድ ሳላህ ህጉን ለማፅደግ ጊዜ የወሰደው ለማሻሻል ብዙ ስለተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ህግ የበቀል ህግ አለመሆኑን ይልቅ የሱዳናውያኑን ደህንነት ለመጠበቅ ወጣ መሆኑን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መናገራቸውን የዘገበው ደግሞ አልጀዚራ ነው፡፡






Post a Comment

0 Comments