የ40 ዓመታት ባላንጣዎቹ የአሜሪካና የኢራን መካረር እልባት ይኖረው ይሆን?



የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ የሁለቱም ፈርጣማ ሃገራት ፍጥጫ ጎልቶ ይታይ እንጂ ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ግን ድፍን 40 ዓመታትን አስቆጥረዋል - አሜሪካና ኢራን፡፡

ሁለቱም ሃገራት መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እርግፍ አድርገው ከተዉበት ከ1980 ወዲህ በአንድም በኩል ጉልበታቸውን ለማሳየት የቃላት ጦርነት ሲወራወሩ በሌላ በኩል ስምምነት ለመፈፀም ሲለሳለሱ ቆይተዋል፡፡

የኢራን እና የአሜሪካ ፀብ ይበልጥ የከረረው ግን ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ነው፡፡

እሳቸው መንበረ ስልጣኑን ከያዙ ወዲህ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ የስልጣን ዘመን የተፈፀመውን የኢራን የኒውክሌር ስምምነት አልቀበልም በማለታቸው ከኢራን ጋር የነበራቸው ቁርሾ ይበልጥ እንዲካረር ምክንያት ሆኗል፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳይደረግ በይፋ ከለከለች፡፡ አሜሪካም በኢራን ላይ ከባድ ያለቻቸውን ማእቀቦችን ጣለች ዙሩም ይበልጥ እየተካረረ ሄደ፡፡

 Getty/ AP

ኢራናውያን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት አምርረው እንደሚጠሉ ቁጣቸውን ገለፁ ለአሜሪካውያኑ ግን ምንም ዓይነት ጥላቻ የለንም ሲሉም እያነቡ መሰከሩ፡፡



የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ዣቫድ ዛሪፈ ኢራን ታጋሽ ነች ፕሬዝዳንት ትራምፕም ትዕቢተኞችን ባይሰሙ ይሻላቸዋል ሲሉ በኤቢሲ ኒውስ በኩል መልእክታቸውን አስተላለፉ፡፡

ቢሆንም ግን ሊስማሙ አልቻሉም፡፡ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ የሁለቱም ሃገራት ውጥረት ይበልጥ እንዲጦዝ የሚያደርግ ክስተት ተተገበረ፡፡ አሜሪካ ኢራን ጀግናየ ምትለውን ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒን ገደለች፡፡ ሁኔታው ለኢራንና ለወዳጆቿ ከባድ መርዶ ሆነ፡፡

ያኔ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ አበጀሁ በሚል አኳኋን ሱሌማኒ የገደልነው ኢራቅ ውስጥ ለሞቱ አሜሪካውያን ወታደሮች ተጠያቂ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡

ፖለቲከኞች ግን የትራምፕን አበጀሁ ማለት ስህተት መሆኑን ነው የሚገልፁት፡፡
«ኢራን የአሜሪካን ልዑላዊነት አጥቅታ አታውቅም። አሜሪካ ሱሌማኒን ጥቃት ያደርስብኛል ብላ በሰው ምድር መግደሏ አግባብነት የለውም። ይህ ማለት አሜሪካ ሕጋዊ ያልሆነ ግድያ ከመፈፀም አልፋ፤ ኢራቅ ውስጥ ያልተገባ ጥቃት ፈፅማለች።» ይላሉ ፖለቲከኞቹ፡፡

ኢራን ለጀነራሏ እና ለጀግናዋ ግድያ አፃፋ ለመመለስ ጊዜ አልፈጀባትም፡፡ ሚሳኤሎቿን ኢራቅ ወደሚገኙት የአሜሪካ የወታደር ስፍራዎች አስወነጨፈች፡፡ አሜሪካ በኢራን ጥቃት ወታደሮቼ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ስትል ኢራን በበኩሏ ጥፊየን በአሜሪካ ፊት ላይ አሳርፌአለሁ የሚል ምላሽ ሰጠች፡፡

የፖለቲካ ጡዘቱ ግን በዚህ ያበቃ አልሆነም ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነ እና 176 ሰዎችን አሳፍሮ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ አየር ላይ ነበረ አውሮፕላን ተከስክሶ የ176ቱም ተሳፋሪዎች ህይወት አለፈ፡፡ ያኔ 63 ዜጎቿን ያጣቸው ካናዳ ጥቃቱ በኢራን ስለመፈፀሙ ማስረጃ አለኝ ስትል ኢራንን ቀውስ አዘችው፡፡


አሜሪካም ጥቃቱ በኢራን የተፈፀመ ስለመሆኑ የቴክኒክ ችግር እንዳልነበረው ገለፀች፡፡

የኢራን ሲቪል አቪየሽን አውሮፕላኑ በቴክኒክ ችግር እንጂ በሚሳኤል ምክንያት አለመከስከሱን ከገለፀ በኋላ በሶስተኛው ቀን አውሮፕላኑ በስህተት በሚሳኤል ተመትቶ እንደወደቀ የአሜሪካ የጦር ጀት እንደመሰላቸው ይፋ አደረጉ፡፡

ያኔ በገዛ ህዝባቸው ውሸታም በሚል ተቃውሞ ገጠማቸው ካናዳና ዩክሬንም ጉዳዩን አወገዙ፡፡ ተቃውሞው በረከተ፡፡ በኢራን የብሪታንያው አምባሳደር በተቃውሞው መሃል ስለምን ተገኙ ስትል ኢራን አምባሳደሩን ለአንድ ሰዓት ካሰረች በኋላ ፈታቻቸው ያኔ ብሪታኒያ ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው ስትል አወገዘች፡፡

በዚህ መሃል የአሜሪካና የኢራን ፍጥጫ ይበልጥ ከርሮ ኢራን ፔንታገንን በጥቁር መዝገቧ ላይ አሰፈረች፡፡

የአሜሪካ መከላከያ የአሸባሪ ቡድን ነው ስትልም ድምዳሜዋን ሰጠች፡፡ የሁለቱም ሃገራት ፍጥጫ የት ያደርስ ይሆን ሲል አለምን ቀልቡ ተሳበ፡፡ ፍጥጫቸው የት ያደርስ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው፡፡






Post a Comment

0 Comments