የመስቀል ደመራ ታሪክ

                     የመስቀል ደመራ ታሪክ


ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ፤ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ 

የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ 300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

326 .. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ 

በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውምአንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽአላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች።

እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 . . ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡

ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 .. ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ዕለት 300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ይከበራል፡፡

                         የደመራ ትርጉም

 

ደመራ የሚለው ቃልደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።

የመረጃው ምንጭ፡- ዓምደ ተዋሕዶ

Post a Comment

0 Comments