በአላማጣ ከተማ አንዲት እናት አራት ልጆችን ተገላገሉ


በትግራይ ደቡባዊ ዞን አላማጣ ከተማ አንዲት እናት አራት ልጆችን መገላገላቸውን የከተማዋ ሆስፒታል አስታወቀ።

በአላማጣ ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ሐኪም ዶክተር ብርሃኑ ነጋሲ እንደተናገሩት ፣ትናንት ሌሊት ስምንት ስዓት አካባቢ በሰላም የተገላገሉት እናት የ32 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው።

ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን የተገላገሉት እናት  በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ  ብለዋል። አንዱ ህጻን ግን በአስጊ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አንደኛው ህጻን አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም፣ ሁለቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸው ሲሆን፣ በአስጊ ሁኔታ ላይ ያለው ህጻን 0 ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም ክብደት እንዳለው አስረድተዋል። ሐኪሙ ”አንድ ጤነኛ ህፃን ሲወለድ ከአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ሊኖረው ይገባል”  ብለዋል።

አሁን የተወለዱት ህፃናት አራት በመሆናቸው ምክንያት ክብደታቸው ቢቀንስም በመልካም ሁኔታ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አራት ልጆች የተገላገሉት እናት ከእነዚህ ሌላ ሁለት ልጆች  እንዳሏቸውም ኢዜአ ዘግቧል።

የሆስፒታሉ  ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ተክላይ በበኩላቸው፣ አራት ልጆች በአንዴ የተገላገሉት እናት  በሆስፒታሉ የቅድመ ወሊድ ክትትል ሲደረግላት ቆይተዋል ብለዋል።



በሆስፒታሉ ውስጥ አንዲት እናት ይህን ያህል ልጆች ስትወልድ  ለመጀመሪያ ጊዜ  መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልፀው፤ ወላዷ ከነልጆቻቸው  አስፈላጊውን እንክብካቤ ተደርጎላቸዋል ብለዋል። አሁን ላይ የተወሰነ የደም መፍሰስ ስላጋጠማቸው ለከፍተኛ ህክምና ወደ መቀሌ ዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደተወሰዱ  ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። 

የመረጃው ምንጭ፡- ኢዜአ 

AS ዘ ብሔረ ጦቢያ

Post a Comment

0 Comments