እያዩ ፈንገስ ቁጥር አንድ - ፌስታሌን | Eyayu Fungus Part One – Festalen

 

       «እያዩ ፈንገስ» ይናገር


የደራሲው አስተዋይነት ከዚህ ይጀምራል። እንደልቡ ይናገር ዘንድ ገጸ ባህሪውን የአዕምሮ ህመምተኛ አደረገው። የአዕምሮ ህመምተኛ የሆኑ ሰዎች እንዴት እንደሚናገሩ አይተናል። እስኪ አዲስ አበባ ውስጥ ጎዳና ላይ ወጥተው ብቻቸውን የሚያወሩ ሰዎችን አስተውሉ፤ የሚናገሯቸው ነገሮች ሁሉ መሬት ላይ ያሉ ናቸው።

ጤነኛ ነው ከሚባለው ሰው የሚለዩት ሀቁን መናገራቸው ነው። የባህል፣ የሃይማኖት ወይም የይሉኝታ ጫና የለባቸውም። እያዩ ፈንገስም እንዲህ ሀቅ ሀቁን ይናገራል። እነዚህ የአዕምሮ ህሙማንን ወደ ጎዳና የሚወጡት በተለያዩ ምክንያት ነው። በህብረተሰቡም የተገፉ ናቸው፤ ይህን የገፋቸውን ህብረተሰብና መንግሥት ጎዳና ላይ ወጥተው ውስጣቸው ያለውን ይናገራሉ።

ኪነ ጥበብ እንዲህ ነው፤ የኪነ ጥበብ ለዛውን ሳይለቅ ሀቁን የሚናገር። ኪነ ጥበብ ከሌላው ዲስኩር የሚለየው ቀጥታ ገለጻ አይደለም፤ የማዝናናት ባህሪም አለው፤ እያዩ ፈንገስ ደግሞ በዚህ የተሳካለት ነው። «ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩትን ያህል ይስቃል» እንደሚባለው «እያዩ ፈንገስ» የልብ የልባችንን ሲነግረን እንስቃለን።

«እያዩ ፈንገስ» ቴአትር ብዙ ተብሎለታል። በ2007 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ተመርቆ ለዕይታ የበቃው ይህ ቴአትር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ መነጋገሪያ ነበር። መነጋገሪያነቱም በአድናቆት ብቻ ነበር። ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው። አንድ፤ ቴአትሩ በአንድ ሰው የሚተወንና ብዙም ያልተለመደ ስለሆነ አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል፤ ቴአትሩ እያዝናና የሚያሳውቅ ነው፤ በአጭሩ ለማድነቅ የሚያስገድድ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት የሚሆነው ግን ወቅቱ ነው። እንደምናውቀው 2008 ዓ.ም ማለት አሁን መጣ ለተባለው ለውጥ እንቅስቃሴ የተሟሟቀበት ነበር። በዚህ ወቅት የግል መገናኛ ብዙኃን በጣም ውስን ነበሩ። በአገሪቱ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጋዜጦች ነበር ያሉት። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም የመንግሥትን እንከን አይናገሩም ነበር።

በዚህ ውስጥ እያዩ ፈንገስ የሚናገራቸው ነገሮች እጅግ አስገራሚ ሆኑ፤ በዚያን ጊዜ መንግሥትን መተቸት አስፈሪ ነበር። ጋዜጠኞችና ጦማሪያን የሚታሰሩበት ነበር፤ በዚህ ውስጥ እያዩ ፈንገስ በብዙዎች ልብ ውስጥ ገባ። ወቅቱ የፖለቲካ ውጥረት የነበረበት ስለሆነ የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ በፖለቲካ ተመነዘሩ። እያዩ ፈንገስ ማህበራዊ ሕይወትን የሚቃኝ እንጂ የፖለቲካ መሣሪያ እንዳልሆነ ደራሲው በአንድ ወቅት ተናግሯል።

ቴአትሩ ደግሞ ደራሲው እንዳለውም ፖለቲካን ብቻ የሚነካ አይደለም፤ ሕዝብን ራሱ ይተቻል፤ ማህበራዊ ሕፀፆቻችንን ይነግረናል። ሰዎች ግን እንደምንም ጠምዝዘው ወደ ፖለቲካ ይወስዱታል።

ደራሲው በረከት በላይነህ ከአሃዱ ኤፍ ኤም 94.3 ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ስለፖለቲካና ኪነ ጥበብ ተናግሮ ነበር። በረከት እንደተናገረው ኢትዮጵያ ውስጥ «ፖለቲካ» የሚለው ቃል ስሙ ጠፍቷል።

ፖለቲካ የማይመለከተው ሰው የለም፤ ፖለቲካ የማይገባበት ቦታ የለውም፤ እንዲያውም «ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ…» በሚለው አገላለጽ አይስማማም። ፖለቲካ ራሱን ብቻ ነጥሎ ያለ ዘርፍ አይደለም፤ በሁሉም ዘርፍ ውስጥ የሚገባ ነው። ትዝብቱንና ምሳሌዎችም ያስቀምጣል።

«ፖለቲካ ውስጥ አልገባም፤ ልጄን ላሳድግበት» ይላሉ ሰዎች። በበረከት እምነት አንድ ሰው ልጁን ማሳደግ የሚችለው በአገሪቱ ሰላም እንዲኖር በመስራት መሆን አለበት። አገር ስትጠፋ እያየ ዝም ካለ ልጁን በሰላም ማሳደግ አይችልም።

በሌላ በኩል ይሄ ሰውዬ መንግሥት የሚያወጣው የሕፃናት ፖሊሲ ይመለከተዋል፤ መንግሥት የሚያወጣው የትምህርት ፖሊሲ ይመለከተዋል። ስለእነዚህ ጉዳዮች ሳያወራ ነው እንግዲህ «ልጄን ላሳድግበት» የሚለው።

እንዲህ እንደ እያዩ ፈንገስ ያሉ ደፈር ያሉ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለምን አይሰሩም ሲባል አንዱ የሚቀርበው

ምክንያት «የመንግሥት አፈና አለ» የሚል ነው። ይህን ሰበብ ብቻ አምኖ መቀበል ግን ትክክል አይሆንም፤ የብቃትና የፈጠራ ችግርም አለ። የታዳሚን ቀልብ ሊይዝ የሚችል መሆን አለበት። ዝም ብሎ «ኢህአዴግ ጨቋኝ፣ ሙሰኛ…» እያሉ ብቻ መሥራትም ከተለመደው የፓርቲዎች ክርክር የተለየ አይሆንም። ልክ እንደ እያዩ ፈንገስ ኪነ ጥበባዊ ለዛውን ይዞ ማህበራዊ ችግሮቻችንን ሁሉ የሚነካካ መሆን አለበት።

ያም ሆኖ ግን የመንግሥት ጫና የለም ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ መንግሥት በገዛ እጁ ይሰደባል፤ ስለተቃራኒ ጾታ የተሰራን የኪነ ጥበብ ሥራ ብድግ ብሎ የፖለቲካ ሽሙጥ ነው ይላል፤ «ግራ» የሚል ቃል ካለበት «ግራ ዘመም» ለማለት ፈልገው ነው ብሎ ያልታሰበ ያስባል። ይሄ ችግር ደግሞ ከከፍተኛ አመራሩ ሳይሆን ከታች ካለው አመራር የሚመጣ አጉል ፍርሃት ነው።

መንግሥትና ኪነ ጥበብን በተመለከተ ደራሲው በረከት በላይነህ ከነገርኳችሁ የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ የተናገረውን አንድ ነገር ጠቅሼ ወደ ቴአትሩ እንሂድ።

መንግሥት ቢያውቅበት ኖሮ ኪነ ጥበብ ማለት ራሱን የሚገመግምበት ትልቅ መሣሪያ ነበር። እንዲያውም ኪነ ጥበብ ባለበት መድረክ እየሄደ አስተያየት መሰብሰብ ይችል ነበር። እዚያ ላይ ያሉ ነገሮች ለፖሊሲ ግብዓት ሊጠቀማቸው ይችላል።

ህብረተሰቡ ምን እያለ ነው፤ መንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዴት ዓይነት ነው የሚለውን ያውቅበታል። አንድ የኪነ ጥበብ ሥራ ላይ ታዳሚው ምን አሳቀው? ምን አስገረመው? ምን አበሳጨው? ምን ሲሆን ነው በደስታ የሚያጨበጭቡት? የሚለውን ማየት የሕዝቡን የልብ ትርታ ይለካበታል።

ወደቴአትሩ ስንመለስ እያዩ ፈንገስ እንግዲህ አራት ዓመታትን ሊያስቆጥር ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሚናገራቸው ሐሳቦች እየተቀነጨቡ በማህበራዊ የመገናኛ አውታሮች የነገር ማጣፈጫ ሲደረጉ ነበር።

ይህ ቴአትር ከለውጡ ወዲህ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የነበረው ቅብብሎሽ ቀንሷል። የቀነሰው ግን ቴአትሩ ቀንሶ ሳይሆን ሰዎች ሌላ አጀንዳ አግኝተው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደፈጉ የሚናገሩባቸው ጋዜጦችና መጽሔቶችም ስለመጡ ሰዎች መንግሥትን የሚተነኩስ ሃሳብ አላጡም። ልብ በሉ! እያዩ ፈንገስ መንግሥትን ተንኳሽ ነው ማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን ሰዎች መንዝረው የሚያወጡት መንግሥትን የምትነካ ቃል ስትነገር ነው።

አሁን የፖለቲካው ለውጥ እንደገና ተቃውሞ እያጋጠመው ነው፤ እያዩ ፈንገስም እንደገና ቃላት ይመነዘሩለት ይሆናል።

ባለፈው ሚያዝያ 27 የተከበረውን የአርበኞች ቀን አስመልክቶ በብሔራዊ ቴአትርና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቴአትር የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ቀርበዋል። እያዩ ፈንገስም በማዘጋጃ ቴአትር ቤት ለ20 ምናምን ያህል ደቂቃዎች ታይቶ ነበር። በዕለቱ ከታየው የቴአትሩ ክፍል ትንሽ ላቃምሳችሁ።

ቴአትሩን በጸጥታ መስማት አይቻልም ነበር። አንድ ቃል በተናገረ ቁጥር የማያቋርጥ ሳቅና ጭብጨባ ይደረጋል። እዚህ ላይ የታዘብኩት ነገር ማንም ሊላቸው የሚችል የተለመዱ ቃላትን ሁሉ ሲናገር ጭብጨባውና ሳቁ ይረብሽ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተዋናዩ ራሱ ግራ ይጋባል፤ መጀመር ያለበትን ሃሳብ ጭብጨባና ሳቅ እስከሚቋረጥ ይጠብቃል፤ ሳይጠበቅ ከተናገረም ምን እንዳለ አይሰማም።

እያዩ ፈንገስ አሁን ከዶክተር አብይ መምጣት በኋላ ያለውን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ይነግረናል። «ዶ.አ.አ.አ.ኮ» የሚል ቡድን አለ ይለናል። «ዶክተር አብይን አትንኩብኝ፣ አትዩብኝ ኮሚቴ» ማለት ነው። ይሄ እንግዲህ ለማህበረሰቡም መሆኑ ነው። ለምን ዶክተር አብይ ይተቻሉ የሚሉ ወገኖች መኖራቸው ደግሞ ግልጽ ነው።

አገሪቱን ደግሞ እንዲህ ይላታል፤

ሲያሻት እምየ

ሲያሰኛት ድንግል

አፍራሽ ያድሳት

አዳሽ ያፈርሳት

የውሃ እናቴን ገደላት እሳት!

ሲመጡ መርከብ ሰብሮ አሻጋሪ

ሲኖሩ ጀልባ ቀዝፎ አሻጋሪ

ሲከራርሙ ዓሣ ነባሪ!

ደራሲው በረከት በላይነህ ገጣሚ ነው፤ ለዚህም ነው እንዲህ ዓይነት ግጥም የጻፈው። ግጥሙ የአገሪቱን የመሪዎች ታሪክ ይነግረናል። አንድ ሥርዓት ሲመጣ ያለፈውን አፍርሶ ነው፤ ያለፈውን ነገር ሁሉ እየኮነነ ነው፤ አገሪቱን እንደገና ነው የሰራኋት ይላል፤ ዳሩ ግን በኋላ ደግሞ እሱም አፍራሽ ሆኖ ይገኛል። ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ የሁሉ ነገር አሻጋሪ ይሆናሉ፤ እየቆየ ሲሄድ «ሰው በላ» ይባላሉ ማለት ነው።

«የአገሪቱ ችግር ግን የ27 ዓመት ችግር ብቻ ነው?» ሲል ይጠይቃል። «ከዘውድ እስከ መለዮ ለባሽ፣ ከባለቁምጣ እስከ ባለሱፍ ሁሉንም አተያያቸው» ይላል። ሁሉም «ተገፋን» ብለው ይመጣሉ፤ ገፍተው ይኖራሉ፤ ተገፍተው ይወድቃሉ። ገለው ይመጣሉ ሞተው ይሄዳሉ። ሁሉም ለነፃነታቸው ያነሱትን ጠመንጃ ነው በኋላ ለነፃነት ማፈኛ ያደረጉት። ሁሉም ሥልጣኑን እስከሚያገኝ ለሕዝብ ይታገላል፤ ሥልጣኑን ሲያገኝ ከሕዝብ ጋር ይታገላል።

«ከሃምሳ ዓመት በላይ ተመሳሳይ ሰበብ! ንጉሡ ባሪያ አመፀብኝ፣ ኤርትራ ጠገበችብኝ፣ ደርጉም ኤርትራ ወነበደችብኝ፣ በዚህ በኩል ወገቤን ቆረጠኝ ሲል፤ ነፃ አውጭ ነኝ ባዩም ሻዕቢያ መጣችብኝ፣ ግንቦት ሰባት አሸበረኝ ሲል…. ቆይ እኔ እምለው! ለንጉሡም፣ ለደርጉም፣ ለነፃ አውጭ ነኝ ባዩም ሻዕቢያ ችግር የሚሆነው እንዴት ብንዝል ነው?»

እያዩ ፈንገስ እንዲህ እንዲህ እያለ ታሪካችንን፣ ፖለቲካችንና ማህበራዊ ኑሯችንን ይነግረናል። ደራሲው በረከት በላይነህ ከተናገረው አንድ መልዕክት እናስቀምጥ! መንግሥት በኪነ ጥበብ የሚነገሩትን ነገሮች ለግብዓት ይጠቀም!

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን

 AS ዘ ብሔረ ጦቢያ

Post a Comment

0 Comments