|
|
የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስከፊ አያያዝና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሻሻል ጠየቀ ።
ፓርላማው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሳዑዲ አረቢያ፣ በኤርትራና በኒካራጓ ውስጥ ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን በተመለከተበት ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ በዚህም በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በማንሳት ነው የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈው።
የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አሁን ድረስ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ሰብአዊ መብቶቻቸው ተጥሶ እንደሚገኝ ጠቅሶ ሁኔታውን አውግዞታል።
ሕብረቱ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሃሳብ ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት ልዑኮች በሳኡዲ አረቢያ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች እንደሚጎበኙ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ሰሚራ ራፋኤላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕብረቱ ለምን አስቸኳይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሰጥ እንዳደረገ ሲያብራሩም፣ ከሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች እየወጡ ያሉ ምስሎችን እንዲሁም ሪፖርቶችን መመልከታቸውንና የስደተኞቹ ጉዳይም እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርትን የጠቀሰው ፓርላማው ከባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አንስቶ በግድ ከየመን ተገፍተው እንዲወጡ የተደረጉ ነፍሰጡር ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው 30 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ያለፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ ሳዑዲ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች እንደሚገኙ አመልክቷል።
ስለዚህም የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አባላት የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡትን ቅድሚያ በመስጠት በአስቸኳይ እንዲለቁ ጥሪ አቅርቧል።
ጨምረውም የሳዑዲ ባለስልጣናት በጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ጎረቤት የመን ሸሽተው ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ሰዎችን ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ተቀብለው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ወደጠበቁ የማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የሕብረቱ ፖርላማ አባል ሰሚራ ራፋኤላ እንደሚሉት የሕብረቱን የውሳኔ ሳኡዲ አረቢያ ስደተኞችን ይዛ የምትገኝበትን ሁኔታ በአፋጣኝ እንድታሻሽል ይጠይቃል።
በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስትም ስደተኞችን ከሳኡዲ አረቢያ በመመለስ ላይ ቢሆንም በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ችግሩ ሰፊ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን