ሀዳ ሲንቄ - የሲንቄ(የ'ዱላ') እናት
በኦሮሞ ባህል ሀዳ ሲንቄ እጅግ የሚደመጡና የሚከበሩ የእርቅ 'ዱላ' የሚይዙ እንስቶች ናቸው።
የሀዳ ስንቄ የተለየችና የተዋበች ዱላ እርቀ ሰላምን ለማውረድ የሚይዟት የፍቅር "ጥይት" ነች። በእሷ የማይረታ ጦረኛ፣ ልቡን ለይቅርታ የማይከፍት ጀግና ቁጣዉን የማያበርድ "ጉልቤ" የለም።
ቀጠን ረዘም ያለችው ሲንቄ(ሲንቄ በኦሮሞ ባህል የተለየች ዱላ ነች) ልክ እንደወንዶቹ ጦር ተሰሚነት ያላቸው የኦሮሞ እናቶች የሚይዟት የስክነት ጦር ናት። ከቁስ በላይ ልዩ፤ ከጠብ መንጃ የላቀች ኃያል ናት።
በሲንቄ፤ ዝናሩን የማይፈታ ጦሩን የማይመልስ ጎበዝ አይገኝም። አንገራግሮም ቢሆን ነገሩን ከማብረድ አያመልጥም።
ሀዳ ሲንቄ ሲንቄዋን ከመሬት ከፍ ከላይ ጎንበስ ካደረገች ለጠብ የመጣዉን አፋቅራ ትመልሳለች።
ጦርነት ቢነሳ፣ በተፈጥሮ ጉዳይ አልያም በፈጣሪ ቁጣ ዝናብ ቢዘገይ ሀዳ ሲንቄ'ዎች' ወደ ወንዝ ወርደው አምላካቸው ያዘገየውን ዝናብ እንዲሰጣቸው እልልል ይላሉ፤ ይማፀኑታልም።
ለዘመቻ የወጣ ጎበዝ በሀዳ ሲንቄ እልልታ ከዘመቻው ይመለሳል።
ሀዳ ሲንቄ በጨሌ ያጌጠውን "ቦኬ" የተባለውን ልብስ ለብሰው፣ እርጥብ ሳር ይዘው፣ በጨሌ የተዋበ ቡርቄ(ቅል)፣ ሲንቄ(ዱላ) ይዘው ደሙ የፈላውን ያሰክናሉ፣ የተቆጣን ያረጋጋሉ፣ የጋለውን ያበርዳሉ።
ባል ሚስቱን ካስቀየመ ሀዳ'ዎች'(እናቶች) ሲንቄ ይዘው ወንዝ ይወርዳሉ፤ ባልም ሚስቱን ላስቀየመበት መካሻ በሬ አርዶ፣ ባለቤቱን ይቅርታ ጠይቆ አዝሎ ወደቤት ይመልሳል። ይህ ካልሆነ ሀዳ ስንቄ'ዎች' በፍፁም ወደ ቤት አይመለሱም። እርቀ ሰላም ሲያወርዱም መቀነታቸውን (ሰበታ ይሉታል) ይፈታሉ።
ሲንቄ ከተለየ የዛፍ ተክል የሚበጅ የእንስቶች ጦር ነው።
ለትዳር የበቃ ጎረምሳ ሚስት ማግባት ሲፈልግ ከልዩ ዛፍ ያዘጋጀውን ሲንቄና የእንጨት ትራስ ለሚያገባት ኮረዳ ይሰጣል። ስጦታዉን እጅ በእጅ አይሰጥም።
ልጅ አባቱን አስከትሎ ወደ ቤት ይገባና ለሚስትነት የታጨቺው ኮረዳ ከኋላቸው ትገባለች። ስጦታዋንም ትረከባለች።
ሀዳ ሲንቄ'ዎች' ጨሌ አዳን ግንባራቸው ላይ፤ ጨሌ ቆሮሮን አንገታቸውና ጆሯቸው ላይ አድርገው ይዋባሉ።
ሀዳ ሲንቄ'ዎች' እንዲህ ናቸው፤ ከፍቅር እንጂ ከጥላቻ ጋር መኖር አይስማማቸውም። በዳይም ተበዳይም ቂማቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ሳይታክቱ ይጠይቃሉ፤ ሲጠይቁም ይደመጣሉ።
"ስልጡን" የመንግሥት የፀጥታ ሰራተኛም ሆነ ሌላ አካል በኦሮሞ ምድር የሀዳ ስንቄን ያህል ሠላምን ማምጣት አይቻለውም።
AS ዘ ብሔረ ጦቢያ
0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን