የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) ሰርክ ገዝፎ የሚንጥ፣ እሩቅ ግን ቅርብ ውብ ስሜት…. አድዋ!!


እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)

በተስፋዬ እሸቱ (ረ/ ፕሮፌሠር)


ከያኒ የአንጻር ጌታ ነው፡፡ የነበረውን፣የሰማውን፣ ያነበበውን የኖረውን ሁነትና እውነት ለመገልበጥ አይታትርም፡፡ ሰው አይቶት፣ ተገንዝቦ የኖረበትን ወይንም እየኖረበት ያለን እውነት አይደግምም፤ ከያኒ፡፡

ለዚህም ነው የከያኒ እውነት ሁሌም አንጻር (point of view) አለው የሚባለው፡፡ በጋራ ያየነውን ሀቅ፣ አምነን እየኖረበት ያለን እውነት፤ እሱ በወደደው፣ በፈለገው መንገድ ሌላ የሚተኮር፣ የሚወደድ፣ ግብ ይሰጠዋል፡፡ የግቡ ትልም ደግሞ አንጻር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የከያኒ እውነት ትናንትን አጣቅሶ፣ ዛሬ እንድንኖርበት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ነገንም እንድንናፍቅ ያስገድደናል፡፡

ከያኒ ሲልቅ፣ ታሪክ ላይ ሌላ እውነት ፈልፍሎ፤ አውዱ ላይ ሌላ ሀቅ አብጅቶ በጉዳዩ  እንድናተኩር፣ አተኩረንም ህይወትን እንድናጣጥም አድርጎ እያዋዛ፤ ረግቶ ከጠነዛ መንፈስ ይፈታናል፡፡

˝አይለወጥም፣ አይነካም ቅዱስ ታሪክ ነው˝ ብለን ከታሰርንበት፣ ሀቅ ብለን ካመለክነው አምልኮ አላቆ ሌላ መንገድ፣ ሌላ ስርየት ያጎናጽፈናል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) አድዋም ነገረ-መሰረቱ፣ ማጠንጠኛ ሀቁ ይሄው ነው፡፡ ሌላ ደግሞ፤…ሌላ እውነት! ሌላ አድማስ! ገዝፎ የሚንጥ፤ እሩቅ ግን ደግሞ ቅርብ ውብ ስሜት፤  የጂጂ አድዋ!

የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) አድዋ፣ ስር እና መንፈሱ  ድሮ ጥንት ተጉዞ፤ የሰው ልጅ ˝ሀ˝ ብሎ ሲፈጠር ከተሰጠው ጸጋና ክብር ይጀምራል፡፡ ˝የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ እያለ እየተጎነጎነ፣ እየተስረቀረቀም፡፡ ሰውን በአምላኩ አምሳያ ፈጠረው የተባለውንም አገናዝባ፤ ˝ሰብዕ የዐቢ እምኩሉ ፍጥረት˝ ያለውን አስታውሳም ነው፡፡ ጂጂ አድዋን፣ ˝የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር˝ ብላ አህዱ ያለችበት መንገድ ታሪከ-አድዋን ያየችበት፣ ሀቁን የተገነዘበችበት እና እንዲተኮር የፈለገችው ትርጓሜ ነው፡፡ 

ተስፋዬ እሸቱ (ረ/ ፕሮፌሠር)


የሰው ልጅ ትልቁ ጻጋ፣ ሰው ሆኖ የመፈጠር፣ ተፈጥሮም በክብር የመኖር ጸጋ ሲገፈፍ ሰው መሆን ˝አዲዎስ!˝ ነው ትላላች ጂጂ በአድዋ ውስጥ ስታስብ፤ ደግሞም ከሩቅ  ስባ በምክንያት ስታመጣም፤ ስትመዝም፡፡ ታዲያ እጅጋየሁ ሽባባው ይህንን የመሰለ የእይታ አድማስ ይዛ ስትመጣ ንቡር ነቃሽም ነበረች ማለት ይቻላል፡፡

የሰው ልጅ ከተሰጠው ክብር አንሶ ሲወርድ፣ ረክሶ ግን ለዘለአለም እንዳይኖር፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መድህን ይሆን ዘንድ፣ አምላክ ሰው ሆኖ  ሞቶ፣ ለሌሎች ምሳሌነትን የገለጸበት፤ "አንዱ፡ስለ፡ዅሉ፡ሞተ"ን  እሷ በአድዋ ˝ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…˝ ብላ አዛምዳዋለች፡፡ እናም የጅግጋየሁ ሽባባው አድዋ ጥንት፣ ድሮ የትየለሌን ከትልቁ መጽሀፍ፣ መጽሀፍ ቅዱስ አጣቅሷል ስል መነሻዬ ይሄው ነው፡፡ 

ይህንን ለሰው ልጅ ቤዛ የመሆንን አስተምህሮት፤ ለሰው መሞት፣ ለሰው ክብር መሰዋት፤ ከምንም በላይ ሰው ክብር መሆኑን  መገንዘብ ነው የአድዋ አባቶቻችን በአፍ ሳይሆን በተግባር ሳያጎድሉ ከወኑት የምትለን ጂጂ፤ በአድዋ፡፡ የጂጂ ንቡር ጠቃሽነትም ወደር የማይገኝለትና  ምክንያታዊ ሆኖ የቀረበው፣ በሙዚቃው ወስጥ ጀግኖች አባቶቻቻን ሰው ልጅ ክብር፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን ተገንዝበውና አስገንዝበው እንዳለፉ አጽንዖት ሰጥታው ታልፋለች፡፡

ይህንን ከላይ የተወሰደ እና ለሰው ክብር ሲባል መሞት ትልቁ የፍቅር መገለጫ በዚህችው አገር፣ በአድዋ ተራራ ሲከወን ˝ በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ…˝ እያለች በድጋሚ፤ ግን ደግሞ በተለየ ገለጻ በደማቁ ከትባው ታልፋለች፤ በሙዚቃ- አድዋዋ፡፡




AS ዘ ብሔረ ጦቢያ

Post a Comment

0 Comments