"እንደ ተንሰፈሰፍንለት ዐይደለም ! ?" ዳኛው ማነው?




የ"ዳኛው ማነው?" መፅሐፍ ሽፋን


"እንደ ተንሰፈሰፍንለት ዐይደለም ! ?"
 
ዳኛው ማነው?


በሀብቱ ግርማ

በኢትዮጵያ የግራ ዘመም ፓለቲካ ውስጥ መካሰሱ አላቆመም፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ በአብዮቱ ዘመን እና በድሕረ የአብዮቱ ዘመን ንቅናቄዎች፣ ግንባሮች እና ፓርቲዎች በሕብረት፣ በልዩነት እና በጦርነት ውስጥ ተጉዘዋል፡፡ 

በዚህ ፍትግትግ ውስጥ ተነበው፣ ተነግረው ያላለቁ ድብቅ ዕውነቶች አሉ፡፡ አንደኛው ዕውነት የብርሃነመስቀል ረዳ÷ ፓለቲካዊ እና ሰውነታዊ ማንነት ነው፡፡ 

ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል የብርሃነመስቀል ረዳን የልጅነት፣ የተማሪነት፣ የዩኒቨርስቲ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ በተለያዩ የአፍሪካ ሐገራት፣ በአውሮፓ እንዲሁም በአብዮቱ ዘመን እና በለውጡ ዘመን ውስጥ የሄደባቸውን የፓለቲካ እና የህይወት መንገድ አቃምሳናለች፡፡ 

1. የብርሃነመስቀል ረዳ የተማሪዎች የትግል ሟሟሻ የሆነውን "መሬት ለአራሹ" የተሰኘውን ቃል "ፈጣሪነት" አስተዋውቃናለች፡፡

2. በትወና፣ በጋዜጠኝነት፣ በፀሐፊነት የነበረውን ክህሎት ነግራናለች፡፡ 

3. ከተማሪነት ትግል እስከ "ስመ ገናናው" የኢትዮጵያ የተማሪዎች ፓርቲ መስራችነቱን አነሳስታልናለች፡፡ ኢህአፓ÷ የብርሃነመስቀል ረዳ የበኩር ልጅ፡፡

4. የብርሃነመስቀል ረዳ እና የታደለች የፍቅር ህይወት በህቡዕ እና በዲስፕሊን ውስጥ ያለውን መልክ አስጎንጭታናለች፡፡ 

5. የብርሃነመስቀል ረዳ ፅሁፎችን ከመፅሐፉ ጋር ተያይዘው መቅረባቸው፡፡ 

6. መፅሐፉ÷ የብርሃነመስቀል ረዳን ግለ ታሪክን በዘጋቢ ፊልም ለማዘጋጀት ብዙ የታሪክ ዕጣፋቶችን በመያዙ÷ መልካም ዕድል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ 

7. ለወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ግን በእስር ቤት ቆይታቸው የገቡትን ቃልኪዳን በማሳካታቸው እና ለተማሪ አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች እና ለኢትዮጵያ የፓርቲ የፓለቲካ ታሪክ አንድ ተጨማሪ ዶሴ በመስጠታቸው እናመሰግናለን፡፡ 

እና 
ሌሎች
 
÷ የፊውዳሉን መንግስት አስወግዶ ከተማሪነት ወደ አብዮት ከዚያም ወደ ዕርስ በርስ ጦርነት በገባው ትውልድ ውስጥ ለጠፋው÷ ለተረፈን ታሪክ ተከሳሽ እና ከሳሾች ለአመታት ቦታ እየተቀያየሩ ተወነጃጅለዋል፡፡ 

ውንጀላውን ለማክሸፍ ወይንም የተለያየ ገፅ ያለውን የታሪክ እልባታቸውን በተለያዩ መረጃዎች እና ማስረጃዎችን አስደግፎ ማቅረብ "ዳኛው ማነው?" የሚለውን ጥያቄ መጠኑ እንዲቀንስ ወይንም የራስን ዕውነት በመረጃዎች ለማቅረብ ይረዳል ብዬ አምናለው፡፡

የብርሃነመስቀል ረዳን ግለ ታሪክንም ሊወጣ ነው ሲባል ተንሰፍስፈን ያነበብንበት ም/ት ተጨማሪ ፓለቲካዊ መረጃዎችን ሁሉን አቀፍ በኾነ ዕይታን ይዞልን ይመጣል ብለን በማሰብ ነው፡፡ 

ከዚህ አንፃር÷ የወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ዳኛው ማነው መፅሐፍ ሳያነሳቸው፣ በደንብ ሳይፈትሻቸው ካለፉት ጉዳዮች አንፃር÷ እንደ ተንሰፈሰፍንለት ሳይሆን እንደቀረ እገምታለው÷ 

1. በአልጄሪያ እና በአውሮፓ በነበረው የተማሪዎች ማህበር (ብኃላም ኢህአፓ እና መኢሶን በሆነው ሕብረት) ውስጥ የነበረው የትግል አደረጃጀት፣ የሐገራዊ ጥያቄዎች አስተሳሰብ እና ልዩነት ውስጥ የነበረው ነጥቦች ተትተዋል፡፡

2. የአብዮቱ መከሰትን አስመልክቶ አይቀረኔትን የኢህአፓ ዲሞክራሲያ፤ የመኢሶንም የሰፊው ሕዝብ ድምፅ ህትመቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡ እነ ብርሃነመስቀል ረዳ÷ ከህቡዕ ወደ ተገለጠ የፓርቲ አደረጃጀት እንዲገባ ለምን እንደዘገዩ ሳይተነተን ታልፋል፡፡ ይህ ክፍተት በመኖሩ ምክንያትም ግራ ዘመም አብዮተኛ መሪዎቹ ብሶት የወለደውን ሰፊውን ሕዝብ ይዘው ሕዝባዊ መንግስት ለማቋቋም የመጀመሪያ ወርቅ ዕድላቸውን ለምን እንዳመለጣቸው በአግባቡ አልተነገረንም፡፡ 

3.  የፊውዳሉ መንግስት የመጨረሻ ጣር ላይ በነበረበት ጊዜ÷ የልጅ እንዳልካቸው፣ የልጅ ሚካኤል እምሩ፣ የኢህአፓ፣ የመኢሶን እንዲሁም የወታደራዊው ጁንታ ትንቅንቆችን ተድበስብሰው ታልፈዋል፡፡ 

በነዚህ ጊዜያት ውስጥ የነበሩትን የወታደሩ ለአብዮቱ የነበረው ድጋፍ፣ የጁንታው የአብዮቱን መጥለፍ፣ የኢትዮጵያ ትቅደም ሐቲት፣ የሕብረተሰባዊነት ሶሻሊስታዊ ርዕዮት፣ የላብ አደሩ/ የወዝ አደሩ/ የሐሳብ እና የቃላት ትንቅንቆችን አልተዳሰሱልንም፡፡

4.   የደርግ መንግስት ለግራ ዘመም ሐይሎች ያቀረበውን የአንድ ሶሻሊስታዊ ሕብረት ጥሪን አስመልክቶ እነ ብርሃነመስቀል ረዳ እና ኢህአፓ የነበራቸውን አመለካከት እና የመኢሶኖቹ ውሳኔ ጋር የነበረውን የሶስትዮሽ ፍትጊያ ከታክቲክ እና ከስትራቴጂ የፓርቲ መዋቅራዊ ውሎች አንፃር በመፅሐፉ በልኩ አልተገለፀልንም፡፡

5. በኢህአፓ ውስጥ የተፈጠረውን የአንጃ ቡድኖች መሰረታዊ ልዩነቶች በልካቸው አልተዳሰሱም፡፡ በከተማው እና በገጠር የትግል ሂደቱ ላይ የነበራቸው ልዩነት በመስመሮች መሀል ሳይገለፅልን ታልፋል፡፡ የእርማት እንቅስቃሴው ሂደትም ድርጊቱን እንጂ መነሻ እና መድረሻ አላማውም አልተገለፀልንም፡፡ 

6. በኢህአፓ፣ በመኢሶን እንዲሁም በኢሰፓ መሀከል የተፈጠረውን የሲቪል ዋር ዕልቂት ከፎኮይዝም፣ ከፓዝሽናል ዋር እንዲሁም ከፕሮትራክትድ ስትራግል አንፃር በጥልቀት ሳይገለፅልን በቀላሉ ታልፋል፡፡ 

7. የብርሃነመስቀል ረዳ እና የኃይሌ ፊዳ መጨረሻ÷ በአንድ ጉድጓድ መፈፀምን አስመልክቶ÷ ከፓለቲካዊ ትራጄዲ አንፃር አልተተነተነም፡፡ በደንብ ሳይዳሰስ ያለፈ ነጥብ ነው፡፡ ብርሃነመስቀል ረዳ በእስር ቤት የፃፈው ሰነድ ለዚህ ታሪክ የነበረውን አይተኬ ሚናም በቀላሉ ሳይካተት ታልፋል፡፡ 

8. ኢህአፓ መደባዊ ትግል የሚያደርግ ድርጅት የነበረ ቢሆንም÷ ዕርስዎ ለብሄረሰባዊ ጉዳዮች የተጋነነ ትኩረት ለሚሰጠው ኢህአዴጋዊ መንግስት በምን ምክንያት የቢሮ ከበርቴውን ሊቀላቀሉ ቻሉ!? (ይህን ጉዳይ እንደ 'ፓኬት ስቶሪ' ቢያስገቡልን ዕወድ ነበር፡፡)

9. ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ልጆቻ፤ ስለ አባታቸው ስለ ብርሃነመስቀል ረዳ ከአደጉ ብኃላ ያላቸውን ጥያቄዎች፣ ስሜቶች ቢካተትልን ኖሮም÷ ሰዋዊ የኾኑ የህይወታችሁን ገፃች ለመረዳት ተጨማሪ ዕድል ይሆነን ነበር፡፡ 

10. ብርሃነመስቀል ረዳ÷ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እና የፓርቲ ታሪክ ውስጥ የስበት ማዕከል ከሆኑ ሰዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ ፓለቲካዊ የጥንካሬ ስብዕናውን ብቻ ሳይሆን÷ ታደለች ኃ/ሚካኤል ሰዋዊ ድክመቱን እና የሚደርስበትን ትችት አዳብለው ቢያቀርቡልን ኑሮ የበለጠ የተወደደ መፅሐፍ ይኾን ነበር እላለው፡፡ 

እና 

ሌሎች

የማስታወሻ ህዳግ፡-

ዳኛው ማነው የሚለው የብርሃነመስቀል ረዳ መፅሐፍ ለተደራሲው እንዲደርስ 40 አመት ፈጅቷል፡፡ ከሀሳብ እስከ ውልደቱ፡፡

ይህን ባዮግራፊ ከጥሬ ሐቆች በላይ ወደ አንድምታዊ/ ትርጋሚያዊ/ የመፅሐፍ ዐይነት ለመቀየር ወርቅ ዕድል እንዳመለጠን ይሰማኛል፡፡ (Academic biography) 

ፀሀፊዋም የመፅሐፉን ርዕስ 'ዳኛው ማነው?' ብለው ከመረጡ÷ ብርሃነመስቀል ረዳ ላይ የሚነሱትን ጥያቆዎች እና የግራ ዘመሙ ዘመን ላይ መስመር÷ በመስመር ተጉዘው ሙግታቸው ማቅረብ ነበረባቸው፡፡  

ነገር ግን ይህንን ክፍተት ለመሙላት በቴሌቭዥን/ በራዲዮ በሚደረጉ ቃለመጠይቆች ለመሙላት ግን እኛ ዕድል፤
እሷቸው ደግሞ አቅሙ እንዳላቸው አምናለው፡፡ 

ከአክብሮት ጋር የተሞነጨረ!




AS ዘ ብሔረ ጦቢያ

Post a Comment

0 Comments