ፕሬዝዳንቱ ወደ ኳታር ያቀኑበት ምክንያት በሃገራቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ከኳታሩ ኢሚር አሚን ቢን ሃማድ አልታኒ ድጋፍ ለማግኘት ቢሆንም ፈጣን ድጋፍ ሳያገኙ በስምምነት ብቻ ተመለሰዋል፡፡
ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ በዳቦ እጥረት እና በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት ቅር የተሰኙ ሱዳናውያን አሁንም ቁጣቸውን በየ አደባባዩ እየገለፁ ነው፡፡
እንዲህ አይነቱ ተቃውሞ አዲሷ ያልሆነው ሱዳን ለተቃውሞው ዘላቂ መፍትሔ ባለመውሰዷ ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ ስልጣን ይብቃ ወደሚል ተለውጧል፡፡
ሱዳንን ካለፉት 29 ዓመታት ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት እየመሯት ያሉት ኦማር አልበሽር ህዝባቸው ስልጣን እንዲለቁ ከጠየቃቸው አንድ ወር አልፏል፡፡
በአንፃሩ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ላይ እንደሚቆዩ መግለፃቸውን ተከትሎ ተቃውሞው እየበረታ መጥቷል፡፡
ፕሬዛዳንቱ ተቃውሞውን የሚፈቱበት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ዶሃ ያቀኑ ሲሆን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል፡፡
የኳታሩ ኢሚር አሚን ቢን ሃማድ አልታኒ ከሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ጋር በነበራቸው ቆይታ በሱዳን ስለሚተገበሩ በርካታ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ተወያይተዋል ብሏል ሱዳን ትሪቡን በዘገባው፡፡
ኢሚሩ በሱዳን ስላለው ቀውስ በተመለከተ በሰፊው እንደተወያዩ ዘገባው አስነብቧል፡፡
የኳታር አቋም ሱዳን እንድትረጋጋ እና አንድነቷ እንዲጠናከር ማገዝ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሱዳን ከሳኡዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከኳታር ጋር የነበራት ግንኙነት ተቋርጦ ነበር፡፡ በወቅቱ ዶሃ የሱዳን የቁርጥ ቀን አጋሯ እንደነበረች በሁኔታውም ቅር መሰኘቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ኳታር ከሌሎች ሃገራት ጋር በመፎካከር በሱዳን ላይ ያላትን ተቀባይነት ለማጠናከር እና የቀይ ባህር ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ያለች ሃገር መሆኗንም ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡

0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን