"የዋልታ ዘገባ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ ነው" የትግራይ ክልል


የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ያስተላለፈውን ''የውሸት ዜና በቸልታ'' አልመለከተውም አለ።

ቢቢሲ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ዋልታ [ኢንፎርሜሽን ማዕከል] ታህሳስ 3 በፌስቡክ ገፁ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት ደህንነትን በማስመልከት ያወጣው ዜና ስህተት መሆኑን ጠቅሶ ወዲያው ይቅርታ ቢጠይቅም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያልፈው ገልጿል።

ቢቢሲ አናገርኳቸው ያላቸው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሳ፤ "ዋልታ ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ የሐሰት ነው" በማለት ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

"ይህ ዘገባ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ሴራ ነው ብለን ነው የምንረዳው። በይቅርታ የሚታለፍም አይደለም" ያሉት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዋ የዚህ አይነት ዘገባ ወዳልተፈለገ ሁከት ሊያስገባ ይችላል ብለዋል።

ዋልታ ታህሳስ 3/2012 ዓ.ም አመሻሽ ላይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ''ባልታወቀ አደጋ ህወታቸው ማለፉን መቀሌ ከሚገኘው ሪፖርተራችን ሰምተናል" ብሎ መዘገቡን ያስታወሰው ቢቢሲ ዋልታ ዜናዉን ከገጹ ላይ ካነሳው በኋላ፤ ''ዜናው ከተቋሙ እውቅና ውጪ'' የተላለፈ እንደሆነና ጉዳዩ እንዴት እንደተፈፀመ አጣርቶ እንደሚያሳውቅ ጠቅሶ ይቅርታ ጠይቋል። ሲል አስነብቧል።

ወ/ሮ ሊያ ካሳ "ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ወደ ዋልታ ደጋግመን ብንደውልም ስልክ ስለማያነሱ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" በማለት ለቢቢሲ መግለፃቸውንም ተጠቅሷል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የዋልታን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ዘግቧል። 

Post a Comment

0 Comments