17 የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልቅ ቀያቸው ሲያመሩ በታጣቂዎች ከታገቱ ሳምታት ተቆጠሩ።
በታጣቂዎች ታግተው ከሚገኙት 17ቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒበርሲቲ ተማሪዎች መካከል 13ቱ ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ከአጋቾቹ ካመለጠች ተማሪ ማወቅ ተችሏል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ የታገቱት ስድስት ታዳጊዎች ለምን ተገደሉ?
"'እኛ ድሆች ነን፤ ገንዘብ ከየት እናመጣለን' እያልን ስንደራደር ነበር" በጠገዴ ታግቶ የተገደለው ታዳጊ አባት
"ከታገቱት መካከል አንዷ ነበርኩ፤ በሦስተኛ ቀኔ አምልጫለሁ" ተማሪ አስምራ ሹሜ
ተማሪ አስምራ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።
"በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነበርኩ። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በመዘጋቱ ወደ ትውልድ አካባቢዬ ተመልሼ አዲስ ዘመን ከተማ ነው ያለሁት።
ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ። መጀመሪያ በአጋቾቹ የተያዝነው 18 ተማሪዎች ነበርን። እኔ ማምለጥ ስለቻልኩ አሁን ታግተው ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ወንዶች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። አሁን ታግተው ያሉት ተመራቂ ተማሪዎች እና የኢንጅነሪንግ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው።
በወቅቱ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ስለነበር ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተው ነበር። እኛም መውጣት አሰብን ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ የሚያስመጣው ዋና መንገድ በመዘጋቱ ከደምቢ ዶሎ በጋምቤላ በኩል አድርገን አዲስ አበባ ለመግባት ወሰንን።
ሁላችንም ከአማራ ክልል አካባቢዎች የመጣን ተማሪዎች ነን።
ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ የ30 ብር ትራንስፖርት ሲሆን እቅዳችን ጋምቤላ አድረን ወደ አዲስ አበባ ነው። ነገር ግን ያሰብነው ቦታ ሳንደርስ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል 'ሱድ' የምትባል ቦታ ላይ ስንደርስ መኪናውን አስቁመው፤ ወጠምሻ ወጣቶች መጥተው አፈኑን። የአፋኞቹ ቁጥር ከእኛ ቁጥር በላይ ነበር።
አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።
እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።
በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።
እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ 'የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት' ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።
'ከታየሁ እኔም እገደላለሁ' ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታታላለን' አሉኝ።
ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም 'በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከልክሉናል' ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ 'የእነርሱ ነው ያዥው' ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።
ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። 'እንከታተላለን' ነው ያሉኝ።
ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን 'መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ' እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።"
የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ምን ይላሉ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸውን ለልጆቹ ደህንነት ስንል ያልጠቀስናቸው የታገቱት ተማሪ ቤተሰቦች፤ ተማሪዎቹ ከታገቱ አንድ ወር አልፏቸዋል ይላሉ። "በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ውስጥ ስልክ ይደውሉ ነበር አሁን ግን ድምፃቸውን ከሰማን ሦስት ሳምንታት አልፈዋል" ይላሉ።
እህቱ እንደታገተችበት የነገረን አንድ ግለሰብ፤ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ሲወጡ፤ እርሱም እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ቢነግራቸውም እነርሱ ግን ከአሁን አሁን ይረጋጋ እያሉ መቆየታቸውን ያስረዳል።
ይህ ግለሰብ እንደሚለው ሰልክ ተደውሎለት እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ስለመታፈናቸው የሰሙት ሕዳር 24፣ 2012 ዓ.ም ነው።
ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት በተማሪዎቹ ስልክ ከዚያ በኋላ 'የአጋቾቹ ነው' ባሏቸው ስልክ ይደውሉላቸው ነበር። ቦታውን ሲጠይቋቸው ግን እንደማያውቁት ነበር ሲነግሯቸው የቆዩት።
"የሆነ ሰዓት ላይ ስልክ ተሰጥቷት የፅሁፍ መልዕክት ላከችልኝ፤ ''አሻና አፋን ገደራ' የሚባል ቦታ ነው ያለነው፤ ለመከላከያ ደውሉና እዚህ አካባቢ ይፈልጉን' ብላ ፃፈችልኝ" ይላል።
በመጨረሻው የስልክ ልውውጣቸው፤ "አሁንም እዚያው ቦታ ነሽ ወይ?" ብሎ ሲጠይቃት "በፊት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ አሁን ቦታ ቀይረናል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የሁለት የሦስት ሰዓት መንገድ በጫካ እንጓዛለን፤ አታገኙንም፤ አሁንም ልትንቀሳቀሱ ነው ተብለናል፤ እስካሁን ባለው ደህና ነን'' ስትል ስልኩን ከዘጋች ወዲህ ወንደም እህቱን በስልክ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።
ከታጋች ተማሪዎች ወላጆች መካከል ሁለት ሰዎች፤ ስለ ልጆቻቸው መረጃ ፍለጋ ወደ ደምቢ ዶሎ ተጉዘው እንደነበረ ይሄው እህቱ የታገተችበት ወንድም ይናገራል።
እሱ እንደሚለው ወደ ስፍራው የሄዱት ሰዎች ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።
ሌላኛዋ የታጋች ተማሪ እህት ደግሞ ወንድሟ፤ በዩኒቨርሲቲ አንድ የአማራ ተወላጅ ተማሪ መገደሉን ተከትሎ ከፍተኛ ስጋት አድሮበት እህቱ ጋር ደውሎ ገንዘብ እንድትልክለት ይጠይቃል።
"የደወለው ቅዳሜ ቀን ስለነበር እስከ ሰኞ እንዲታገስ ነገርኩት" ትላለች።
"ሰኞ ዕለት ብር ልልክለት ስደውል ስልኩ አይሰራም። የዛኑ ቀን ደውሎ መያዛቸውን ነገረኝ። ከተያዙ ሁለት ሳምንት ድረስ ይደውሉ ነበር ከዚያ በኋላ ግን ድምፃቸው አልተሰማም"
እስካሁን የምንችለውን ነገር ሁሉ እያደረግን ነው የምትለው የተማሪው እህት፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የምታገኛቸው የታጋች ወላጆች በከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ትናገራለች።
"አንጀታቸውን በገመድ አስረው መሬት ላይ ተኝተው ይፀልያሉ፤ ሞተው ከሆነ አስክሬናቸው ይምጣልን" እያሉ ነጋ ጠባ እያለቀሱ ነው ትላለች።
ተማሪዎቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸውና እየተሰቃዩ እንደሚገኙ መስማታቸውንም አክላለች።
የአጋቾቹ ፍላጎት ምንድነው?
ወንድሟ የታገተባት እህት ከወንድሟ ባገኘችው መረጃ መሠረት አጋቾቹ ገንዘብ አይፈልጉም።
ከአጋቾቹ እጅ ያመለጠችው አስምራ እንደምትናገረው፤ አጋቾቹ በተደጋጋሚ "ከእናንት ጋር ጸብ የለንም። ጸባችን ከመንግሥት ጋር ነው" እንደሚሉ ትናገራለች።
አጋቾቹ "የአማራ ህዝብ ልጆቻችን ታግተዋል ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፤ መንግሥት እኛን ያነጋግራል። የዛኔ እኛ ጥያቄያችንን ለመንግሥት እናቀርባለን፤ ጥያቄያችንም ይመሳል" እንዳሉ አስምራ ትናገራለች።
የመንግሥት አካላት ምላሽ?
ኦሮሚያ
የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ "ምንም አይነት መረጃ የለኝም። እኔ የሰማሁት ነገር የለም" ይላሉ።
ጉዳዩ እርሳቸው የሚመሩት ቢሮን በቀጥታ የሚመለከት መሆኑን በመጥቀስ ስለጉዳይ እንዴት መረጃ ሳይኖራቸው እንደቀረ የተጠየቁት ኮሎኔል ገረሱ፤ "እኔ ምንም አልሰማሁም ነው የምልህ። ለምድነው የምትጠይቀኝ?" በማለት መልሰዋል።
የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች የሉም ብለዋል።
ኃላፊው ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም ከማለት ውጪ ማብራሪ መስጠት አልሰጡም።
አማራ
የአማራ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገርም፤ "አሁን ማውራት የማልችልበት ቦታ ነው ያለሁት" በማለት የእጅ ስልካቸውን ዘግተውታል። አቶ አገኘው ተሻገርን መልሰን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከአምስት ቀናት በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ "አራት ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ መረጃው አለኝ" ማለታቸው ይታወሳል።
ታግተው የሚገኙት ተማሪዎች በወላጆቻቸው ጋር በስልክ አልፎ አልፎ እንደሚገናኙ ጭምር ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ተማሪዎቹ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ከአባ ገዳዎች፣ ከአከባቢው ማህብረሰብ እና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት እያደረግን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረትም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ አልተሳካም።
ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የወሰደው የለም በማለት በርካቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
ከእነዚህ መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ትናንት ባወጣው መግለጫ የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ እና ጥቃት አድራሾቹ ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
'የታገቱት ተማሪዎች ይለቀቁ' የሚል ዘመቻ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተካሄዱ ነው፤ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥም እየተጠየቀ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትሩን ካቢኔዎች 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን በማስታወስ፤ በደህንነት ስጋት የዩኒቨርሲቲ ግቢ ለቀው ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ የታገቱ ሴት ተማሪዎች ትኩረት አለማግኘት በመጠቀስ ብስጭት አዘል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ምንጭ ቢቢሲ
0 Comments
ሐሳቦን ያጋሩን